2ኛው ንግግር፡ ሶሻሊዝም

ሶሻሊዝም

ዛሬ እዚህ ቦነስ አይረስ ከተማ የኢኮኖሚ ነጻነት ስርጭት ማዕከል እንግዳ ሁኜ ተገኝቻለሁ። የኢኮኖሚ ነጻነት ማለት ምን ማለት ነው? የኢኮኖሚ ነጻነት ስርአት ትርጉም ምንድን ነው? መልሱ ቀላል ነው፦ የገበያ ኢኮኖሚ ነው፤ የሰዎች ትብብር እና ማህበራዊ ስራ ክፍፍል በገበያ የሚወሰንበት ስርአት ማለት ነው። ይህ ገበያ ቦታ አይደለም፤ ሂደት እንጂ። ግለሰቦች በመግዛት እና በመሸጥ፣ በማምረት እና በመሸመት ለአጠቃላዩ የማህበረሰብ አስራር አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ስርዓት ነው።

የዚህ የገበያ ኢኮኖሚ ስርአት ጋር በተያያዘ “የኢኮኖሚ ነጻነት” የሚለውን ቃል የምንጠቀም ቢሆንም ብዙ ግዜ ሰዎች ለዚህ ቃል ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ ነው። የኢኮኖሚ ነጻነትን ከሌሎች ነጻነቶች ለይተው ይቆጥሩታል። ለአስፈላጊነታቸው አብላጫ የሚሰጧቸውን እነዚህን ነጻነቶች የኢኮኖሚ ነጻነት ባልተከበረበት ሁኔታ እነሱን ለይቶ ማስከበር የሚቻል ይመስላቸዋል። የኢኮኖሚ ነጻነት ትርጉም ይህ ነው፦ ግለሰብ ራሱን ከጠቅላላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር የሚያዋህድበትን መንገድ ራሱ መምረጥ የሚችልበት ስርዓት ነው። ግለሰብ የስራ መስኩን መምረጥ ይችላል። መስራት የሚፈልገውን ሙያ የመስራት ነጻነት አለው።

በእርግጥ ይህ የነጻነት ትርጉም ዛሬ አብዛኘው ሰው ከሚሰጠው ትርጉም ይለያል። ይህ ትርጉም የሰው ልጅ በኢኮኖሚ ነጻነት አማካኝነት ከተፈጥሮዓዊ ተጽእኖዎች ነጻ እንደሚወጣ ይናገራል። በተፈጥሮ ውስጥ ነጻነት ተብሎ ሊጠራ የሚችል ምንም ነገር የለም፤ ያለው ብቸኛ ነገር የተፈጥሮ ህጎች መደበኝነት ሲሆን አንድ ነገር ማሳካት የፈለገ ሰው እነዚህን የተፈጥሮ ህጎች ከመከተል ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም።

ማህበረሰብ ውስጥ ያለ ነጻነት

የሰው ልጅን አስመልክተን ነጻነት የሚለውን ቃል ስንጠቀም በተለምዶ የምናስበው በማህበረሰብ ውስጥ ስለሚገኝ ነጻነት ነው። ይሁን እንጂ ዛሬ የማህበረሰብ የነጻነት አይነቶች በብዙ ሰዎች ዘንድ የተነጣጠሉ ተደርገው ይቆጠራሉ። ዛሬ እራሳቸውን “ነጻ ሃሳቢ”(liberal) ብለው የሚጠሩ ሰዎች የሚያራምዷቸው ፖሊሲዎች ከአስራዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የነጻ ሃሳቢዎች የነጻነት ፖሊሲዎች ጋር ሲነጻጸሩ ፍጹም ተቃራኒ ናቸው። የዛሬዎቹ ነጻ ሃሳቢ ተብዬዎች የመናገር ነጻነትን፣ የሃሳብ ነጻነትን፣ የጋዜጣ ነጻነትን፣ የሃይማኖት ነጻነትን እንዲሁም ከፍርድ ውጭ ከሚደረግ የእስር ነጻነትን ሲያነሱ እነዚህን ሁሉ ነጻነቶች ኢኮኖሚያዊ ነጻነት በሌለበት ሁኔታ ጠብቆ ማቆየት የሚቻል ይመስላቸዋል። ያልተረዱት ነገር ገበያ በሌለበት እና መንግስት ሁሉንም ነገር በሚቆጣጠርበት ስርአት ውስጥ እነዚህ ሁሉ ነጻነቶች በህግ የተቀመጡ ወይም በህገመንግስት የሰፈሩ ቢሆኑ እንኳ የህልም እውነታ መሆናቸውን ነው።

ስለ አንድ ነጻነት ነጥለን እናንሳ፤ የጋዜጣ ነጻነት። ማተሚያ ቤቶች በሙሉ በመንግስት ባለቤትነት ስር በሆኑበት ስርአት ምን መታተም እንዳለበት እና እንደሌለበት የሚወስነው አካል መንግስት ነው። መንግስት ማተሚያ ቤቶችን በተቆጣጠረበት እና ለእትም የሚበቃውን እና የማይበቃውን በሚወስንበት ስርአት የመንግስት ሃሳቦችን የሚቃወሙ ሃሳቦች ለእትም የመድረስ እድል አይኖራቸውም። የጋዜጣ ነጻነት ይጠፋል። የሌሎቹም ነጻነቶች እጣፈንታም ተመሳሳይ ነው።

በገበያ መር ኢኮኖሚ ግለሰብ የሚፈልገውን ሙያ የመምረጥ ነጻነት አለው፤ ራሱን ከማህበረሰቡ ጋር የሚያዋህድበትን መንገድ ራሱ የመምረጥ ነጻነት አለው። በሶሻሊስት ስርአት ግን ይህ እውን አይሆንም። የግለሰብ ሙያ በመንግስት አዋጅ ይወሰናል። መንግስት የማይፈልጋቸውን ሰዎች ከሚኖሩበት ስፍራ አፈናቅሎ ሌላ የሀገር ክፍል እንዲሄዱ የማስገደድ ስልጣን ይኖረዋል። መንግስትን በመቃወም ዝነኛ የሆነን አንድ ሰው ለመንግስት አስቸጋሪ ከሆነበት ስፍራ አፈናቅሎ 5ሺህ ኪሎሜትር ርቆ እንዲኖር የማድረግ ስልጣን መንግስት ይኖረዋል።

በዘይቤያዊ እይታ ካየነው ሰው በገበያ መር ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ነጻነት እንከን የሌሽ ነጻነት አለመሆኑ እርግጥ ነው። ነገር ግን እንከን የለሽ ነጻነት የሚባል ነገር የለም። ነጻነት ትርጉም ሊያገኝ የሚችለው በማህበረሰብ እይታ ብቻ ነው። ከአስራስምንተኛው ክፍለዘመን ደራሲያን መሃል “የተፈጥሮ ህግ” ደራሲያን የነበሩት ሰዎች(ከሁሉም በላይ ጆን ጃክ ሩሶ) ሰው በጥንት ዘመን “ተፈጥሮአዊ” ነጻነት ነበረው ብለው ያምኑ ነበር። እውነታው ግን በነዚያ ጥንት ዘመናት የሰው ልጅ ነጻ አልነበረም፤ ሰው ከእሱ በላይ ጠንካራ በሆኑ ሰዎች ምህረት ስር ነበር። “ሰው ነጻ ሁኖ ይወለዳል፤ ሁሉም ቦታ ግን በሰንሰለት ታስሮ ይታያል” የሚለው የሩሶ ታዋቂ አባባል ለሰሚው አስደሳች ቢሆንም እውነታው ግን ሌላ ነው፤ ሰው ነጻ ሁኖ አይወለድም። ሰው ሲወለድ በጣም ደካማ ጡት ጠቢ እንስሳ ነው። የወላጆቹን ጥበቃ ሳያገኝ፣ ወላጆቹ ደግሞ የማህበረሰብን ጥበቃ ሳያገኙ ሰው ህይወቱን ማቆየት አይችልም።

በማህበረሰብ ውስጥ ነጻነት ማለት ሰው በሌሎች ሰዎች ላይ በሚተማመነው ደረጃ ሰዎች በሱ ይተማመኑበታል ማለት ነው። በገበያ መር ኢኮኖሚ እና በኢኮኖሚ ነጻነት ስርዓት የሚመራ ማህበረሰብ፣ ሰው የወንድም ዜጋው አገልጋይ የሆነበት እና ወንድም ዜጋው የሱ አገልጋይ የሆነበት ማህበረሰብ ነው። የገበያው መር ኢኮኖሚ ከሁሉም ሰው መልካም ፍቃድ እና ድጋፍ ውጭ የሆኑ አለቆች የሚገኙበት ስርዓት እንደሆነ ብዙ ሰዎች ያምናሉ። የኢንዱስትሪ አለቆች፣ ነጋዴዎች እና ስራ ፈጣሪዎች የኢኮኖሚው ስርዓት እውነተኛ አለቆች ተደርገው ይቆጠራሉ። ይህ ግን የህልም እውነታ ነው። የኢኮኖሚው ስርአት እውነተኛ አለቆች ሸማቾች ናቸው። ሸማቾች ደንበኝነታቸውን ከአንድ የንግድ ቅርንጫፍ ሲያቋርጡ እነዚህ ነጋዴዎች በኢኮኖሚው ስርአት ከደረሱበት ከፍ ያለ ደረጃ ይወድቃሉ ወይም አካሄዳቸውን በማስተካከል ወደ ሸማቹ ፍላጎት እና ትእዛዝ መልሰው መጠጋት ይኖርባቸዋል።

እመቤት ፓስፊልድ የኮሙኒዝምን ሃሳብ ከሚያሰራጩ ዝነኛ ሰዎች መሃል ተጠቃሽ የነበረች ስትሆን ቢያትሪስ ፖተር በሚለው የመጀመርያ ስሟ እና ታዋቂ በነበረው ባለቤትዋ ሲድኒ ዌብ አማካኝነት ዝነኝነትን አትርፋለች። ይህች እመቤት የታዋቂ ነጋዴ ልጅ የነበረች ሲሆን በታዳጊ እድሜዋ የአባቷ ጸሃፊ ሁና ሰርታለች። በግለ ታሪክ መጽሃፏ እንደሚከተለው ትጽፋለች፦ “በአባቴ ንግድ ውስጥ ሁሉም ሰው እሱ የሚያስተላልፈውን ትእዛዝ ማክበር ነበረበት። የሁሉ አለቃ እሱ ነበር። ብቸኛ አዛዥ እሱ ነበር። ለእሱ ግን ትእዛዝ የሚሰጠው ሰው የለም።” ይህ ግን ነገሩን በጣም በአጭር እይታ መመልከት ነው። አባቷ የሸማቾች እና የገዢዎች ትእዛዝ ተቀባይ ናቸው። አለመታደል ሁኖ ግን እሷ እነዚህን ትእዛዞች ማየት አልቻለችም። የሷ ትኩረት በአባቷ ቢሮ ወይም ፋብሪካ ውስጥ ስለሚተላለፈው ትእዛዝ ብቻ ስለነበር በገበያ መር ኢኮኖሚ ውስጥ ስለሚከናወነው ነገር ጠለቅ ብላ አልፈተሸችም።

በሁሉም የኢኮኖሚ ችግር ረገድ የታላቁን ፈረንሳዊ ኢኮኖሚስት የፍሬድሪክ ባስትያት ቃላትን ልብ ማለት ይኖርብናል። ከባስትያት ድንቅ ጽሁፎች መሃል አንዱ “የማይታየው እና የሚታየው” የሚለው ጽሁፉ ነው። የአንድ የኢኮኖሚ ስርዓትን አሰራር ለመረዳት ትኩረት መስጠት ያለብን ለሚታዩን ነገሮች ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ለማይታዩም ነገሮች ጭምር ነው። ለምሳሌ አንድ አለቃ ለቢሮ ተላላኪ የሚያስተላልፈው ትዕዛዝ በክፍሉ ለሚገኝ ለማንኛውም ሰው ይሰማል። የማይሰማው ትእዛዝ ግን ሸማቾች ለአለቃው የሚያስተላልፉት ትእዛዝ ነው።

አለቆቹ ሸማቾች ናቸው

እውነታው በካፒታሊስት ስርአት ስር የመጨረሻዎቹ አለቆች ሸማቾች ናቸው። ሉዓላዊ የሆነው አካል መንግስት ሳይሆን ሰዎች ናቸው። ሉዓላዊነታቸውም የሚረጋገጠው የማይረባ ውሳኔ የመወሰን መብት ባለቤቶች በመሆናቸው ነው። ይህ ነው የሉአላዊ ሰው ልዩ መብት። ስህተት የመስራት መብት ነው። ስህተት ከመስራት ማንም ሊያግደው ባይችልም ለስህተቶቹ ግን ዋጋ የሚከፍለው እሱ ራሱ ነው። ሸማቹ ሉዓላዊ ነው ወይም የበላይ ነው ስንል ሸማቹ ከስህተት ነጻ ነው እያልን አይደለም፤ ሁሌም ለራሱ የሚጠቅመውን ነገር ያውቃል እያልን አይደለም። ሸማቾች ብዙ ግዜ መግዛት እና መጠቀም የሌለባቸውን ነገሮች ገዝተው ሲጠቀሙ እናያለን።

ነገር ግን በካፒታሊስት ስርዓት የሚመራ መንግስት ለሽያጭ የሚቀርቡ ነገሮችን በመቆጣጠር ሰዎች ራሳቸው ላይ ሊያደርሱት ከሚችሉት ጉዳት መከላከል ይችላል የሚለው ሃሳብ የተሳሳተ ነው። የመንግስት ስልጣን እንደ የአባትነት ስልጣን የሚታይበት እና መንግስት የሰዎች ሞግዚት የሆነበት ሀሳብ የሶሻሊዝም ደጋፊዎች ሃሳብ ነው። ከተወሰኑ አመታት በፊት የአሜሪካ መንግስት “ክቡር ሙከራ”(a noble experiment) በሚል ስያሜ ያሚታወቀውን ህግ ተግብሮ ነበር። ይህ ክቡር ሙከራ አስካሪ መጠጥን መግዛትንም ሆነ መሸጥን ሕገወጥ የሚያደርግ ሕግ ነበር። ብዙ ሰዎች ብራንዲን እና ዊስኪን ከመጠን በላይ የሚጠጡ መሆናቸው እውነት ነው፤ ይህንንም በማድረጋቸው እራሳቸውን ሊጎዱ ይችላሉ። አንዳንድ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ማጨስን እንኳ ይቃወማሉ። ማቆም እያለባቸው በአጫሽነት የሚቀጥሉ እና ከልክ በላይ አጫሽ የሆኑ ብዙ ሰዎች መኖራቸው እርግጥ ነው። ይህ ግን ከኢኮኖሚ ውይይት ባሻገር የሚሄድ ጥያቄን ያስነሳል:- የነጻነትን እውነተኛ ትርጉም ያሳያል።

እርግጥ ነው፣ ከመጠን በላይ መጠጣት ወይም ማጨስ ከሚያስከትለው ጉዳት ሰዎችን መከላከል ጥሩ ነገር ነው። ግን ይህንን የተቀበልን ግዜ ሰዎች እንደዚህ ማለት ይጀምራሉ፡ አካል ሁለመናችን ነውን? የሰው አእምሮ የበለጠ አስፈላጊ አይደለምን? እውነተኛው የሰው ልጅ ስጦታ፣ እውነተኛው የሰው ልጅ ገጽታ አእምሮው አይደለምን? ለአካል ፍጆታ የሚሆኑ ነገሮች ላይ የመወሰን መብት ለመንግስት ከሰጠነው፣ በማጨስ ወይም ባለማጨስ እና በመጠጣት ወይም ባለመጠጣት ላይ መንግስት የመወሰን መብት ካለው የሚከተለውን ጥያቄ ለሚያነሱ ሰዎች ጥሩ መልስ አይኖረንም፦ “የሰው ልጅ አእምሮ እና መንፈስ ከስጋው በላይ አስፈላጊ በመሆናቸው የሰው ልጅ ራሱን ይበልጥ ሊጎዳ የሚችለው መጥፎ መጽሃፍ በማንበብ እና መጥፎ ሙዚቃ በማዳመጥ ነው። ስለዚህ መንግስት እነዚህን ስህተቶች ሰዎች እንዳይፈጽሙ የመከላከል ግዴታ አለበት።”

እናም እንደሚታወቀው ለምዕተ አመታት መንግስታት እና ባለስልጣናት ተልእኳቸው ይህ ነበር የሚመስላቸው። ይህም ደግሞ የሩቅ ዘመናት ክስተት ብቻ አይደለም። ረጅም ከማይባል ግዜ በፊት ጀርመን የምትተዳደረው ጥሩ እና መጥፎ ስዕሎችን የመለየት ስራ ተልእኮው ባደረገ መንግስት ነበር። በተግባር ግን ይህ የስዕል ጥራት የመለየት ስራ ይሰራ የነበረው በወጣትነት እድሜው በቪየና ውስጥ በሥነ-ጥበባት አካዳሚ የመግቢያ ፈተናውን በወደቀው እና የስዕል ፖስትካርድ ሰአሊ በነበረው በራሱ በአዶልፍ ሂትለር እይታ መሰረት ነበር። በዚህም መሰረት የከፍተኛ አስተዳዳሪውን የኪነጥበብ እና የስዕል እይታ የሚጻረር ሃሳብ መናገር ህገወጥ ሁኖ ነበር።

የአልኮል ፍጆታዎን መቆጣጠር የመንግስት ግዴታ መሆኑን መቀበል ከጀመሩ፣ የመጻህፍት እና የሃሳቦች ቁጥጥር ይበልጥ አስፈላጊ ነው ለሚሉ ሰዎች ምን መልስ መስጠት ይችላሉ?

ነጻነት ማለት ስህተት የመስራት ነጻነት ማለት ነው። ይህንን መገንዘብ አለብን። ወገኖቻችን ገንዘባቸውን የሚያጠፉበትን እና ህይወታቸውን የሚመሩበትን መንገድ ልንተች እንችላለን። ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ፍጹም ሞኝነት እና መጥፎነት የሚንጸባረቅበት ነው ብለን ልናምን እንችላለን ነገር ግን ነጻ ህብረተሰብ ውስጥ ወገኖቻቸው አኗኗር ዘይቤያቸውን እንዴት መለወጥ እንደሚገባቸው ሰዎች አስተያየት የሚሰጡባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። መጽሐፍ መጻፍ ይችላሉ፣ መጣጥፍ መጻፍ ይችላሉ፣ ንግግር ማድረግ ይችላሉ፣ ከፈለጉ መንገድ ዳር ጭምር መስበክ ይችላሉ፤ ሰዎች ይህንንም ሲያደርጉ በብዙ ሀገር ይታያሉ። ነገር ግን ሰዎች ማድረግ የሌለባቸው ነገር ቢኖር አንድን ነገር የመከወን ነጻነት ሌሎች እንዳይኖራቸው ስለፈለጉ ብቻ ሀይልን በመጠቀም ከተግባሩ ለመከልከል መሞከር ነው።

የመደብ ማህበረሰብ

በባርነት እና በነጻነት መሃል ያለው ልዩነት ይህ ነው። ባርያው አለቃው ያዘዘውን ማድረግ አለበት። ነጻ ዜጋ ግን የህይወቱን መስመር የሚመርጥበት ሁኔታ ላይ ይገኛል(የነጻነት ትርጉም ይህ ነው)። የካፒታሊስት ስርአት በአንዳንድ ሰዎች አግባብ ላልሆነ ጥቅም ሊውል እንደሚችል(እየዋለም መሆኑ) እርግጥ ነው። መደረግ የሌለባቸውን ነገሮች የማድረግ ነጻነት በእርግጥ ይሰጣል። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች የአብዛኛው ማህበረሰብ ድጋፍ ያላቸው ሲሆኑ ሁኔታውን የሚቃወም ሰው የወገኖቹን ሃሳብ ማስቀየር የሚችልበት መንገድ አለው። ሊያሳምናቸው ይችላል፣ ሊያግባባቸው ይችላል። ነገር ግን የመንግስትን የፖሊስ አቅምን ወይም ሀይልን በመጠቀም ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ አይችልም።

በገበያ ስርአት ውስጥ ሁሉም ሰው ወገኑን የሚያገለግለው እራሱን በማገልገል ነው። የማህበረሰብ ቡድኖች እና ግለሰቦች ስለሚጋሩት ሁለንተናዊ የተሳሰረ ጥቅም የአስራስምንተኛው ክፍለዘመን ደራሲዎች ሲያወሩ ይህን ማለታቸው ነው። እናም ይህን የጥቅም መተሳሰር ሀሳብን ነው ሶሻሊስቶች የሚቃወሙት። ሶሻሊስቶች በተቃራኒው በተለያዩ ቡድኖች መሃል ስለሚታየው “እርቅ አልባ የጥቅም ግጭት” ያወሩ ነበር።

ይህ ምን ማለት ይሆን? ካርል ማርክስ በኮሙኒስት ማኒፌስቶ መጽሃፉ በመጀመርያው ምዕራፍ የተለያዩ የማህበረሰብ መደቦች ሊታረቅ በማይችል የግጭት ሁናቴ ይኖራሉ ያለ ሲሆን ለሃሳቡ ግን ድጋፍ የሚሰጥ ምሳሌ ማቅረብ አልቻለም ነበር። የሰጣቸው ምሳሌዎች ከቅድመካፒታሊዝም ማህበረሰብ የተወሰዱ ነበሩ። በቅድመካፒታሊዝም ዘመን ማህበረሰብ በዘር መደብ የተከፈለ ነበር። በህንድ ሀገር አንድ የዘር መደብ “ካስት(caste)” በሚለው ስያሜ ይታወቃል። ለምሳሌ በመደብ ማህበረሰብ ውስጥ ሰው ፈረንሳዊ ሁኖ አይወለድም፤ የፈረንሳይ መኳንንቶች አባል ወይም የፈረንሳይ መሃከለኛ መደብ(bourgeoisie) አባል ወይም የፈረንሳይ አርሶ አደሮች አባል ሁኖ ይወለዳል። በመሃከለኛው ክፍለዘመን ግዜ ደግሞ ባርያ ሁኖ ይወለዳል። እስከ የአሜሪካ አብዮት ድረስ ባርነት በፈረንሳይ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም ነበር። በሌሎች የአውሮፓ ግዛቶች ሲጠፋም ከዛ ዘግይቶ ነው።

ነገር ግን የባርነት ስርዓት ከሁሉም ቦታ በላይ በአስከፊ ገጽታ የተመዘገበበት(የባርነት ስርአት መሻሩንም ተከትሎ) በእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች ስር ነበር። ግለሰብ ከወላጆቹ የወረሰውን የኑሮ መደብ ሙሉ ህይወቱን ይዞት ይኖራል። ለልጆቹም ያስተላልፋል። ሁሉም መደብ ልዩ መብት እና አስከፊ ገጽታ ነበረው። የላይኛው መደብ ልዩ መብት ብቻ የሚያጣጥም ሲሆን ዝቅተኛው መደብ አስከፊ ገጽታ ብቻ ነበር የሚያስተናግደው። ከሌላው መደብ ጋር በሚደረግ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ከመሳተፍ ውጭ አንድ ሰው በመደቡ ምክንያት የሚደርስበትን ህጋዊ በደል የሚቀርፍበት ሌላ መንገድ አልነበረውም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በባርያ ባለቤቶች እና በባርነት በሚኖሩ ሰዎች መሃል እርቅ አልባ የጥቅም ግጭት አለ ማለት ይቻላል ምክንያቱም ባሮች የሚፈልጉት ባርነታቸውን ማጥፋት ነው። ይህ ግን ለባርያ ባለቤቶቹ ኪሳራ ነው። በዚህም ምክንያት በማህበረሰብ መደቦች መሃል እርቅ አልባ የጥቅም ግጭት መኖሩ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ እውነታ ነው።

መርሳት የሌለብን ነገር የአውሮፓ እና አውሮፓውያን በአሜሪካ ባቋቋሙት ቅኝ ግዛቶች ውስጥ የማህበረሰብ ስርዓቱ የመደብ ስርዓት በነበረበት በዛ ዘመን ሰዎች የሀገራቸው ዜጋ ከሆኑት የሌላው መደብ አባላት ይልቅ በሌላ ሀገር ከሚኖሩ የመደባቸው ሰዎች ጋር የላቀ የዝምድና ስሜት ይሰማቸው ነበር። የፈረንሳይ መኳንንት አባል የሆነ ሰው የታችኞቹን መደብ ፈረንሳውያን የሀገሩ ወገን አድርጎ አያስባቸውም ነበር፤ ለሱ ሊወደዱ የማይችሉ ተራ ህዝቦች ነበሩ። እንደ እኩያው የሚቆጥረው የሌሎች ሀገሮች(ለምሳሌ የጣልያን፣ የእንግሊዝ እና የጀርመን) መኳንንቶችን ብቻ ነው።

የዚህ ሁኔታ ግልጽ ማሳያ የግዜው የአውሮፓ መኳንንቶች ተመሳሳይ ቋንቋ መጠቀማቸው ነው። ይህ ቋንቋ ፈረንሳይኛ ሲሆን ከፈረንሳይ ውጭ በሚገኙ ዝቅተኛ የማህበረሰብ መደቦች መሃል መግባብያ ቋንቋ አልነበረም። የመሃከለኛው መደብ አባላት የራሳቸው ቋንቋ የነበራቸው ሲሆን የአርሶ አደሩ ማህበረሰብ የአነጋገር ዘይቤ ደግሞ ለሌላው ማህበረሰብ ክፍል ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ቋንቋ ነበር። የሰዎች አለባበስም በተመሳሳይ ሁኔታ ይለያይ ነበር። እ.አ.አ በ1750 ዓ.ም ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ የሚጓዝ ሰው፣ በመላው አውሮፓ የላይኛው ማህበረሰብ መደብ የነበሩት መኳንንቶች አለባበሳቸው ተመሳሳይ እና ከታችኛው ማህበረሰብ መደብ የሚለይ መሆኑን ያስተውላል። መንገድ ላይ ያገኘኸውን አንድ ሰው በቅጽበት ከአለባበሱ የየትኛው ማህበረሰብ አባል እንደሆነ ማወቅ ትችላለህ።

ይህ ሁኔታ በአሁኑ ዘመን ካለው ሁኔታ የሚለይበትን መንገድ ማሰብ ይከብዳል። እኔ ከአሜሪካ ወደ አርጀንቲና ከመጣሁ በኋላ መንገድ ላይ የማየው ሰውን የማህበረሰብ ደረጃ በአለባበሱ መገመት አልችልም። ልገምት የምችለው ነገር ቢኖር የአርጀንቲና ዜጋ መሆኑን እና በህግ የተገለለ የማህበረሰብ አባል አለመሆኑን ነው። ይህ ሁኔታ በካፒታሊዝም አማካኝነት የመጣ ስርአት ነው። እርግጥ በካፒታሊዝም ስርአትም ውስጥ የሀብት ልዩነት ይስተዋላል። ምንም እንኳ የተሳሳተ አመለካከት እያራመዱ ቢሆንም የማርክስ ተከታዮች ይህ ልዩነት በድሮው የመደብ ስርዓት ስር ከነበረው ልዩነት አይተናነስም ይላሉ።

ማህበረሰባዊ ተንቀሳቃሽነት

በካፒታሊዝም ስርዓት እና በሶሻሊዝም ስርዓት የሚስተዋሉት ልዩነቶች አንድ አይደሉም። በመሃከለኛው ክፍለዘመን(በብዙ ሀገሮች ደግሞ ከዛም ከረጅም ግዜ በኋላ) አንድ የመኳንንት ወይም የመሳፍንት ቤተሰብ ጥራቱ፣ ችሎታው፣ ጥሩነቱ እና ባህሪው ምንም ሆነ ምን በመቶዎች ለሚቆጠሩ አመታት ትልቅ ሀብት ይዞ በመሳፍንትነት ሊዘልቅ ይችላል። የዘመናዊው የካፒታሊዝም ስርአት ግን ሶሾሎጂስቶች “ማህበረሰባዊ ተንቀሳቃሽነት” ብለው የሚጠሩት ክስተት የሚስተዋልበት ነው። እንደ ጣልያናዊው ሶሾሎጂስት እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ቪልፍሬዶ ፓሬቶ ከሆነ የማህበረሰባዊ ተንቀሳቃሽነት ቁልፍ መርህ “የማህበረሰብ ቁንጮዎች ተለዋዋጭነት(la circulation des élites)” ነው። ይህ መርህ ሁልግዜም በማህበረሰብ መሰላል ላይ በቁንጮነት የሚቀመጡ ሀብታሞች እና የፖለቲካ መሪዎች እንደሚገኙ ቢናገርም በዚህ ቁንጮ ቦታ ላይ የሚቀመጡት ሰዎች(elites) ሁሌም ተለዋዋጭ እንደሆኑ ያስረዳል።

በካፒታሊስት ማህበረሰብ ውስጥ ያለው እውነታ ይህ ነው። ነገር ግን በቅድመ ካፒታሊዝም ዘመን ይህ ሁኔታ እውን አልነበረም። የቀደምት ዘመናት ታላቅ የመኳንንት ቤተሰቦች እና የዛሬዎቹ የመኳንንት ቤተሰቦች ተመሳሳይ ናቸው። የዛሬ መኳንንቶች ከዛሬ ከስምንት መቶ ወይም ከሺህ አመታት በፊት ከነበሩ መኳንንቶች የተዋረዱ ናቸው። የአርጀንቲና የረጅም ግዜ ገዢ የነበሩት የቦርቦን ካፒቴኖች ሀገሪቱን ከአስረኛው ክፍለዘመን ጀምሮ የገዙ ንጉሳዊ ቤተሰብ ናቸው። እነዚህ ንጉሳን ዛሬ ኢሌዴፍራንስ(Île-de-France) ተብሎ በሚታወቀው ግዛት ላይ ግዛታቸውን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማራዘም ችለዋል። በአንጻሩ በካፒታሊስት ማህበረሰብ ውስጥ የማያቋርጥ የማህበረሰብ ተንቀሳቃሽነት አለ። ድሆች ሀብታም ይሆናሉ፣ የሀብታም ዘር ልጆች ሀብታቸውን በማጣት ድሃ ይሆናሉ።

በአስራዘጠነኛው ክፍለዘመን አውሮፓ በግዙፍ የንግድ ድርጅት መሪነት ከፍተኛ እውቅና እና ዝና ስላተረፈ ሰው ህይወት ታሪክ የሚዘግብ መጽሃፍ ዛሬ በቦነስ አይረስ መሃከለኛ መንገድ በሚገኝ የመጽሃፍ መደብር ውስጥ አገኘሁ። የሰውየው ዝና ምድር ተሻጋሪ ከመሆኑ የተነሳ ህይወት ታሪኩ እዚህ ሀገር ለንባብ መብቃት ችሏል። አጋጣሚ ሁኖ ከዚህ ሰው የልጅ ልጅ ጋር ትውውቅ አለኝ። ከአያቱ ጋር ተመሳሳይ ስም አለው። ኑሮን በብረት አንጥረኛነት የጀመረው አያቱ ከሰማኒያ ዓመታት በፊት የተቀበለውን የመኳንንት ማዕረግ ልጁ አሁን የመልበስ መብት ቢኖረውም ዛሬ ልጁ ኒው ዮርክ ከተማ የሚኖር ድሃ ፎቶግራፍ አንሺ ነው።

የዚህ ፎቶ አንሺ አያት ከአውሮፓ ታላቅ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች አንዱ በሆነበት ሰአት በድህነት ይኖሩ የነበሩ ሌሎች ሰዎች ዛሬ የኢንዱስትሪ ካፒቴን ሁነው እናገኛቸዋለን። ሁሉም ሰው የኑሮ ደረጃውን የመቀየር ነጻነት አለው። ሁሉም ሰው መድረስ የሚፈልግበት ደረጃ ካልደረሰ እራሱን ብቻ ተጠያቂ በሚያደርግበት በካፒታሊስት ስርዓት እና በመደብ ስርዓት መሃል ያለው ልዩነት ይህ ነው።

እስካሁን ድረስ ከሁሉም ታዋቂው የሃያኛ ክፍለዘመን የኢንዱስትሪ ባለሙያ ሄንሪ ፎርድ ነው። ከጓደኞቹ በተበደረው ጥቂት መቶ ዶላሮች በመጀመር በአጭር ግዜ ውስጥ በአለም ላይ እጅግ በጣም አስፈላጊ ከሚባሉት የንግድ ድርጅቶች አንዱን አቋቋመ። በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደዚህ አይነት ታሪኮችን በየቀኑ ማግኘት ይቻላል።

ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የሙታንን ህይወት ታሪክ የሚዘግብ ረጅም እትም በየቀኑ ይዞ ይወጣል። እነዚህን ታሪኮች በምታነቡበት ግዜ በኒው ዮርክ መንገዶች በጋዜጣ አዟሪነት ኑሮን ስለጀመረ የታዋቂ ነጋዴ ታሪክ ሊያጋጥማቹህ ይችላል። ወይም ኑሮን በቢሮ ተላላኪነት ጀምሮ በህይወቱ መጨረሻ ኑሮን በታችኛው የደረጃ ዘንግ በጀመረበት በዛው የባንክ ድርጅት ውስጥ ፕሬዝዳንት ሁኖ እናገኘዋለን። በእርግጥ ሁሉም ሰው የዚህ ደረጃ ከፍታ ላይ አይደርስም። ሁሉም ሰው ግን መድረስ አይፈልግም። ግዜያቸውን ለሌሎች ችግሮች ትኩረት በመስጠት ማሳለፍ የሚፈልጉ ሰዎች ያሉ ሲሆን ለነዚህ ሰዎች በፊውዳል ማህበረሰብ ወይም በመደብ ማህበረሰብ ውስጥ ክፍት ያልነበሩ እድሎች ዛሬ ክፍት ናቸው።

የመንግስት እቅድ አውጭነት

የሶሻሊስት ስርአት በተቃራኒው የራስን ሙያ የመምረጥ ነጻነትን ለሰው ይከለክላል። የሶሻሊስት ስርዓት አንድ የኢኮኖሚ ባለስልጣን ብቻ ያለበት ስርዓት ሲሆን ይህ ባለስልጣን ምርትን በሚመለከቱ ጉዳዮች በሙሉ የመወሰን መብት አለው።

የኛን ዘመን ለየት ከሚያደርጋቸው ነገሮች መሃል አንዱ፣ ሰዎች ለተመሳሳይ ነገር የተለያየ ስም መጠቀማቸው ነው። የሶሻሊዝም እና የኮሙኒዝም አዲሱ ስም “እቅድ” ነው። ሰዎች ስለ “እቅድ” ሲያወሩ “ማዕከላዊ እቅድ” ማለታቸው ሲሆን ትርጉሙም በመንግስት የታቀደ አንድ እቅድ ማለት ነው። ከመንግስት ውጭ በሆነ አካል የሚደረግን እቅድ የሚከለክል አንድ እቅድ።

አንድ የከፍተኛ ምክር ቤት አባል የሆነች የብሪታንያ እመቤት “እቅድ ወይም ምንም እቅድ(Plan or No Plan)” የሚል በአለም ዙርያ እውቅናን ያተረፈ መጽሃፍ ጽፋለች። የመጽሃፏ ርዕስ ትርጉም ምንድን ነው? እሷ “እቅድ” ስትል ያሰበችው በሌኒን፣ በስታሊን እና ተተኪዎቻቸው የሚደረገውን እቅድ እና የአንድ ሀገር ዜጎችን ሙሉ አኗኗር የሚያስተዳድረውን እቅድ ነው። ስለሆነም የዚህች ሴት ማዕከላዊ እቅድ የግለሰቦችን ግላዊ እቅድ የሚሽር ነው። በዚህም ምክንያት “እቅድ ወይም ምንም እቅድ” የሚለው አርእስቷ አሳሳች እና አታላይ ነው። ያሉት አማራጮች ማዕከላዊ እቅድ ወይም ምንም እቅድ ሳይሆን መንግስታዊ ባለስልጣን ያወጣው አጠቃላይ ማዕከላዊ እቅድ ወይም ግለሰቦች የራሳቸውን እቅድ የሚያወጡበት ነፃነት ናቸው። አንድ ግለሰብ ለራሱ ህይወት በየቀኑ እቅድ ያወጣል፤ በፈለገም ግዜ እቅዱን መቀያየር ይችላል።

ነጻ ሰው ፍላጎቱን ለማሟላት በየቀኑ ያቅዳል። ለምሳሌ አንድ ሰው “ትላንት ሙሉ ህይወቴን በኮርዶባ ውስጥ እሰራለሁ ብዬ አስብ ነበር” ሊል ይችላል። አሁን ግን ቦነስ አይረስ ስለሚገኘው የተሻለ ሁኔታ ይሰማና እቅዱን በመቀየር “ኮርዶባ ከምሰራ ይልቅ ቦነስ አይረስ ብሄድ ይሻለኛል” ይላል። የነጻነት ትርጉሙ ይህ ነው። ግን እሱ ተሳስቶ ሊሆን ይችላል። ቦነስ አይረስ መሄድ የተሳሳተ ውሳኔ ሊሆን ይችላል። ኮርዶባ ያለው ሁኔታ ለሱ የሚሻል ሁኖ ይሆናል ግን የመጨረሻው ወሳኝ እራሱ ነው።

በመንግስት እቅድ ስርዓት ስር ግን ሰው በሰራዊት ውስጥ እንዳለ ወታደር ነው። ሰራዊት ውስጥ ያለ ወታደር የሚዘምትበትን ስፍራ እና የሚያገለግልበትን ቦታ የመምረጥ ነጻነት የለውም። ትእዛዝ ተቀባይ ብቻ ነው። ካርል ማርክስ፣ ሌኒን እና ሁሉም ሶሻሊስት መሪዎች እንደሚያውቁት እና እንደሚያምኑት የሶሻሊስት ስርዓት ማለት ሙሉ የምርት ስርአቱ በወታደራዊ አይነት አስተዳደር የሚቀየርበት ነው። ማርክስ ስለ ”ኢንዱስትሪ ሰራዊት” የተናገረ ሲሆን ሌኒን ደግሞ “የሁሉም ነገር አደረጃጀት(የፖስታ ቤት፣ የፋብሪካ እንዲሁም የሌሎች ኢንዱስትሪዎች) በሰራዊት ምስል ይሁን” በማለት ተናግሯል።

በዚህም ምክንያት በሶሻሊስት ስርአት ውስጥ ሁሉም ነገር ከፍተኛ ባለስልጣን በሆኑ ሰዎች ጥበብ እና ተሰጥኦ ይወሰናል። የበላይ አምባገነኑ ወይም የሱ ኮሚቴ የማያውቀው ነገር ግምት ውስጥ አይገባም። ነገር ግን የሰው ልጅ በረጅም ታሪክ ያከማቸው እውቀት በሁሉም ሰው ውስጥ አይገኝም። በምዕተ አመታት ሂደት በጣም ከፍተኛ የሆነ የሳይንስ እና ቴክኒካዊ እውቀት ያከማቸን በመሆኑ ምንም ከፍተኛ ተሰጥኦ ያለው ሰው እንኳ ይህን ሁሉ እውቀት መያዝ አይችልም፤ ከአንድ ሰው አቅም በላይ የሆነ ነገር ነው።

ሰዎች ይለያያሉ፣ እኩል አይደሉም። ይህ ልዩነት ሁሌም የሚኖር ነገር ነው። አንዳንድ ሰዎች በአንድ ርዕስ የበለጠ ተሰጥኦ ያላቸው ሁነው በሌላ ርዕስ ደግሞ ያነሰ ችሎታ ይኖራቸዋል። አንዳንድ ሰዎች አዲስ መንገድ የማግኘት እና የእውቀት አቅጣጫን የመቀየር ተሰጥኦ አላቸው። በካፒታሊስት ማህበረሰብ ውስጥ ቴክኖሎጂ እና ኢኮኖሚ ወደፊት የሚራመዱት በነዚህ ሰዎች አማካኝነት ነው። ሰው አዲስ ሃሳብ ሲኖረው የሃሳቡን እንድምታ የመረዳት ብልጠት ያላቸውን ሰዎች ይፈልጋል። የሃሳቡን እንድምታ የሚረዱ እና ወደፊት የማየት ድፍረት ያላቸው ካፒታሊስቶች ሃሳቡን ወደ ተግባር መቀየር ይጀምራሉ። ሌሎች ሰዎች መጀመርያ ላይ “እነሱ ሞኝ ናቸው” ሊሉ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ ሞኝነት ነው ያሉት ስራ ደስተኛ ሸማቾች አፍርቶ ማለምለም ሲጀምር ከአስተያየታቸው ይቆጠባሉ።

በሌላ በኩል በማርክስ ስርዓት ስር አዲስ ሃሳብ ከመዳሰሱ እና ከሞጎልበቱ በፊት በከፍተኛ የመንግስት አካል አመኔታ ማግኘት ይገባዋል። ነገር ግን የመፍቀድ ስልጣን ያላቸው ሰዎች በስልጣን ቁንጮ ላይ ያሉ ሰዎች በመሆናቸው አዲስ ሃሳብ ተግባር ላይ ማዋል በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። እናም እነዚህ ሰዎች(ወይ በስንፍና እና በሽምግልና ምክንያት ወይ ብሩህ እና የተማሩ ባለመሆናቸው) የአዲሱን ሃሳብ ጠቃሚነት መረዳት ካልቻሉ አዲስ ፕሮጀከት መተግበሩ ይቀራል።

ከውትድርና ታሪክ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። በእርግጠኝነት ናፖሊዮን በውትድርና ጉዳዮች በጣም ብልህ ሰው ነበር። ነገር ግን መፍታት የተሳነው የአንድ ችግር ሰለባ በመሆኑ የመጨረሻ እጣፈንታው ሽንፈት እና በቅድስት ሄለና ደሴት የብቸኝነት ስደት ነበር። የናፖሊዮን ችግር “እንግሊዝን እንዴት ማሸነፍ እችላለሁ?” ማለቱ ነው። ይህንን አላማ ለማሳካት የእንግሊዝን ሰርጥ የሚያሻግረው የባህር ኃይል ያስፈልገው ነበር። በግዜው ይህንን ሽግግር ለማሳካት የሚያስችል መንገድ እንዳላቸው የሚነግሩት ሰዎች ነበሩ። በሚቀዘፉ መርከቦች ዘመን የሞተር መርከብ ሃሳብ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ እነዚህ ሰዎች። ናፖሊዮን ግን የቀረበለትን ሃሳብ ሊረዳው አልቻለም።

ሌላው ደግሞ ጀነራልስታብ(Generalstab) ተብሎ የሚጠራው ታዋቂው የጀርመን ጄነራሎች ስብስብ ነው። ይህ ስብስብ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት በወታደራዊ ጥበብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የለሽ የሚባል ነበር። የፈረንሳዊው የጄነራል ፎክ ስብስብም ቢሆን ተመሳሳይ ዝና ነበረው። ነገር ግን በጄኔራል ፎክ መሪነት ጀርመንን ያሸነፉት ፈረንሳዮቹም ሆኑ ጀርመኖቹ የአየር በረራ ለወታደራዊ ዓላማ ያለውን አስፈላጊነት አልተገነዘቡም። የጀርመን የጄነራሎች እንዲህ ይሉ ነበር፦ “የበረራ ጥቅም ለደስታ ብቻ ነው፤ መብረር ለሥራ ፈት ሰዎች ጥሩ ነው። ከወታደራዊ እይታ አንጻር ጥቅም ያላቸው ዜፕሊኖች(Zeppelins) ብቻ ናቸው።” የፈረንሳይም ጄነራሎችም ሃሳብ ተመሳሳይ ነበር።

በኋላ በአንደኛው እና በሁለተኛው የአለም ጦርነቶች መሃል በነበረው ግዜ ለቀጣዩ ጦርነት በረራ በጣም አስፈላጊ ነው ብሎ የሚያምን ጄነራል በአሜሪካ ውስጥ ይገኝ ነበር(ጄነራል ቢሊ ሚቼል)። ግን በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ሌሎች ባለሙያዎች ሁሉ ተቃወሙት። ሊያሳምናቸው አልቻለም። ለማሳመን የምትሞክራቸው ሰዎች በችግሩ መቀረፍ በቀጥታ ተጠቃሚ የማይሆኑ ከሆነ በጭራሽ ስኬታማ አትሆንም። ይህ እውነታ ይዘታቸው ኢኮኖሚያዊ ላልሆኑ ችግሮችም ተመሳሳይ ነው።

በድህነት ለመቀጠል የተገደድነው ህዝብ ስራችንን በሚገባው ደረጃ ስላላደነቀልን ነው ሲሉ የሚማረሩ ሰዓሊዎች፣ ገጣሚዎች፣ ጸሃፊዎች እና የሙዚቃ አቀናባሪዎች አሉ። በእርግጥ ህዝብ ለጥበብ ስራ ያለው ግምት ከተገቢው በላይ ደካማ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እነዚህ አርቲስቶች “መንግስት ታላቅ አርቲስቶችን፣ ሰአሊዎችን እና ጸሃፊዎችን መደገፍ አለበት” ሲሉ በፍጹም ተሳስተዋል። ለስራው አዲስ መጤ የሆነውን ሰው ጎበዝ ሰዓሊ መሆኑን የመወሰን ስራ መንግስት ለማን ሊሰጥ ይችላል? ሁሌም ወደኋላ ለሚመለከቱት እና አዲስ ፈጠራን የማወደስ ተሰጥኦአቸው ወደተገደበው የጥበብ ተቺዎች እና የጥበብ ታሪክ ፕሮፌሰሮች መንግስት ፊቱን ማዞር ይኖርበታል። ሁሉም ሰው የራሱን እቅድ የማቀድ እና የመተግበር ነጻነት ባለው ስርዓት እና በመንግስት እቅድ ስርዓት መሃል ያለው ትልቅ ልዩነት ይህ ነው።

እውነት ነው በእርግጥ ታላላቅ ሰዓሊዎች እና ታላላቅ ጸሐፊዎች ብዙ ጊዜ ግዙፍ መከራዎችን መቋቋም ነበረባቸው። በጥበባቸው ስኬታማ ሆነውም የሚገባቸውን ገንዘብ ሳያገኙ ቀርተዋል። ቫን ጎህ በእርግጠኝነት ታላቅ ሰዓሊ ነበር። ለመቋቋም አስቸጋሪ የሆነ መከራ ካሳለፈ በኋላ በመጨረሻ በሰላሳ ሰባት አመቱ ራሱን አጠፋ። በሙሉ ህይወቱ አንድ ስዕል ብቻ ነበር መሸጥ የቻለው፤ እሱንም ለአጎቱ ልጅ። ከዚህ አንድ ሽያጭ በቀር በወንድሙ ገንዘብ ነበር የሚተዳደረው። ወንድሙ አርቲስት ወይም ሰዓሊ ባይሆንም የሰዓሊን ፍላጎት ይረዳ ነበር። ዛሬ ግን የቫን ጎህን ስዕል ከአንድ መቶ ወይም ከሁለት መቶ ሺህ ዶላር በታች መግዛት አይታሰብም።

በሶሻሊስት ስርዓት ስር የቫን ጎህ እጣፈንታ ምናልባት የተለየ ይሆናል። አንድ የመንግስት ሹም ይህ ሙሉ በሙሉ በአእምሮው ያልነበረ ወጣት ልጅ ድጋፍ የሚገባው ጎበዝ ሰዓሊ ስለመሆኑ ታዋቂ ሰዓሊዎችን ይጠይቅ ነበር።(ቫን ጎህ የወቅቱን ሰዓሊዎች እንደ እውነተኛ አርቲስት አይቆጥራቸውም ነበር)። እነሱም ያለምንም ጥርጥር “አይ እሱ ሰዓሊ አይደለም። አርቲስት አይደለም። ቀለም የሚያባክን ሰው እንጂ” የሚል መልስ ይሰጡና እጣፈንታው ወደ ወተት ፋብሪካ ወይም የአእምሮ ህሙምተኞች ቤት መላክ ይሆን ነበር። ስለዚህ ይህ በሰዓሊዎች፣ ገጣሚዎች፣ ሙዚቀኞች፣ ጋዜጠኞች እና ተዋንያን ዘንድ እያደገ ያለው የሶሻሊዝም ድጋፍ በተሳሳተ እምነት ላይ የተመሰረተ ነው። ይህንን ያነሳሁበት ምክንያት የሶሻሊዝም እሳቤ ጭፍን ድጋፍ ከሚያገኝባቸው መስኮች መሃል እነዚህ ቡድኖች ዋነኛ ተጠቃሽ በመሆናቸው ነው።

ኢኮኖሚያዊ ስሌት

እንደ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ከካፒታሊዝም እና ከሶሻሊዝም መምረጥ ሲኖርብን የተለየ አይነት ችግር ያጋጥመናል። የሶሻሊዝም ደራሲዎች ኢንዱስትሪ እና የዘመናዊ ንግድ እንቅስቃሴዎች በስሌት ላይ የተመሰረቱ ናቸው የሚል ጥርጣሬ አልነበራቸውም። በስሌት የተመሰረተ እቅድ የሚያወጡት መሃንዲሶች ብቻ አይደሉም። ነጋዴዎችም በስሌት መንቀሳቀስ አለባቸው። የነጋዴ ስሌቶች ሙሉ በሙሉ በሚከተለው እውነታ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፦ በገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሸቀጦች ዋጋዎች ለሸማቹ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለአምራቹም አካል መልእክት ያስተላልፋሉ። የገበያ ዋጋዎች ለአምራቹ ማህበረሰብ ስለ ምርት ግብዓቶች ብዛት እና አዋጭነት አስፈላጊ መረጃ ይሰጣሉ። የገበያው ዋና ስራ በመጨረሻው ሸማች እጅ የሚገባው ምርት ላይ የወጣውን ወጪ ማስላት ብቻ ሳይሆን ከመጀመርያው እርምጃ ጀምሮ የወጣውን ወጪ ጭምር ማስላት ነው። የገበያው አጠቃላይ ስርዓት በያንዳንዱ አምራች ነጋዴ መካከል ካለው የስራ ክፍፍል እውነታ ጋር የሚያያዝ ነው። እነዚህ ነጋዴዎች የምርት ግብዓቶችን(ጥሬ እቃዎች፣ ማሽኖች እና መሳሪያዎችን) ለራሳቸው ለመውሰድ እርስ በእርስ ይጫረታሉ። ከዚህም ባሻገር ለሰራተኞቻቸው በሚከፍሉት ደመዎዝም እርስ በእርስ ይጫረታሉ ማለት ይቻላል። በገበያው የሚወሰን ዋጋ በሌለበት ስርዓት የዚህ አይነት የንግድ ስሌት ሊካሄድ አይችልም።

በሶሻሊስቶች ፍላጎት መሰረት ገበያውን ከናካቴው ካጠፋን መሃንዲሶች እና ቴክኖሎጂስቶች ያሰሏቸውን ስሌቶች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ አደረግን ማለት ነው። ቴክኖሎጂስቶች ከተፈጥሮ ሳይንስ እይታ ሊተገበሩ የሚችሉ ረጅም የፕሮጀክቶች ዝርዝር ሊሰጡን ይችላሉ። ነገር ግን ከኢኮኖሚክ እይታ ከነዚህ ፕሮጀክቶች አዋጭ የሆኑትን ለመለየት አምራች የሚያደርገው የንግድ ስሌት እጅግ አስፈላጊ ነው።

እዚህ እያነሳሁት ያለሁት ዋና ሀሳብ የካፒታሊስት የኢኮኖሚ ስሌት ከሶሻሊዝም ጋር የሚነጻጸርበትን መሰረታዊ ርዕስ ነው። እውነታው የኢኮኖሚ ስሌት እና ሁሉም የቴክኖሎጂ እቅዶች ሊካሄዱ የሚችሉት የገንዘብ ዋጋ ለሽያጭ ለሚቀርቡ ምርቶች ብቻ ሳይሆን ለምርት ግብዓቶችም ጭምር መስጠት ሲቻል ነው። ይህ ማለት ለጥሬ እቃዎች ፣ በከፊል ለተመረቱ ምርቶች፣ ለሁሉም መሳሪያዎች እና ማሽኖች እንዲሁም ለሁሉም የሰው ልጅ ጥረት እና አገልግሎት ሁሉ ገበያ ሊኖረው ይገባል ማለት ነው።

ይህ እውነታ ሲረጋገጥ ሶሻሊስቶች የሚሰጡት መልስ አልነበራቸውም። ለአንድ መቶ ሃምሳ አመታት “በአለም የምናያቸው ክፋቶች በሙሉ በገበያ እና በገበያ ዋጋ ምክንያት የመጡ ናቸው” ሲሉ ቆይተዋል። “የገበያውን ስርዓት ከገበያ ኢኮኖሚ ጋር አንድላይ አጥፍተን በምትኩ ዋጋ እና ገበያ የሌለበት ስርዓት እናቋቁማለን” ይላሉ። ማርክስ “የሸቀጣሸቀጥ ባህሪ(commodity character)” ብሎ የሰየመውን እና የሸቀጣሸቀጦች እና የሰው ልጅ ጥረት አካል የሆነውን ገጽታ ማጥፋት ይፈልጋሉ።

ይህ አዲስ ችግር የተጋረጠባቸው የሶሻሊዝም ደራሲዎች በመጨረሻ መልስ ሲያጡ “ገበያውን ሙሉ በሙሉ አናጠፋውም፤ ገበያ እንዳለ እናስመስላለን፤ ልጆች ትምህርት ቤት ብለው እንደሚጫወቱት የይስሙላ ገበያ ብለን እንጫወታለን።” ግን ልጆች ትምህርት ቤት እያሉ ሲጫወቱ ትምህርት እየተማሩ አይደለም። በማንኛውም ነገር ላይ “ጨዋታ” እያሉ ማስመሰል ይቻላል።

ይህ ችግር በጣም ከባድ እና የተወሳሰበ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ለመዳሰስ እዚህ ካለኝ ግዜ በላይ ያስፈልገኛል። በጽሁፎቼ በዝርዝር አብራርቼዋለሁ። በስድስት ንግግሮች ሙሉ ገጽታውን መዳሰስ የምችለው ችግር አይደለም። በሶሻሊዝም ስር እቅድ እና ስሌት ማውጣት አለመቻሉን በተመለከተ ይበልጥ መዳሰስ ከፈለጋችሁ ወደ ስፓኒሽ ቋንቋ ተተርጉሞ የታተመውን “Human Action” የሚለውን መጽሃፌን አንብቡት።

እናም ኢኮኖሚክ ስሌትን አስመልክቶ በኖርዌያዊው ኢኮኖሚስት ትሪግቭ ሆፍ የተጻፈውን መጽሃፍ እኒሁም ሌሎች መሰል መጽሃፍቶችን አንብቡ። የአንድ ወገን ወገንተኛ መሆን ካልፈለጋችሁ የፖላንድ ኢኮኖሚስት የሆነውን እና በድሮ ግዜ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እና የፖላንድ አምባሳደር ሁኖ አገልግሎ ወደ ፖላን የተመለሰውን የኦስካር ላንግን ታዋቂ የሶሻሊስት መጽሃፍ አንብቡ።

“የሶቭየት ሙከራ”

“የሩስያስ ጉዳይ? ስለዚህ ጥያቄ ሩሲያውያን ምን እያደረጉ ነው?” ብላቹህ ልጠይቁኝ ትችላላቹህ። ይህ ችግሩን ይቀይረዋል። ሩስያውያን የሶሻሊስት ስርዓታቸውን የሚያስተዳድሩበት አለም ለምርት ግብዓቶቻቸው እና ለጥሬ እቃዎቻቸው የገበያ ዋጋ ያለበት አለም ነው። በዚህም ምክንያት ለእቅዳቸው የአለምን ዋጋዎች መጠቀም ይችላሉ። እናም በሩስያ የኢኮኖሚ ሁኔታ እና በአሜሪካ የኢኮኖሚ ሁኔታ መሃል ባሉ ልዩነቶች ምክንያት አሜሪካውያን እንደ አዋጭ የማይቆጥሯቸው ግን በሩስያውያን እይታ አዋጭ እና ተገቢ ተብለው የሚታሰቡ በርካታ ነገሮች አሉ።

“የሶቭየት ሙከራ” ምንም የሚያረጋግጠው ነገር የለም። የሶሻሊዝም መሰረታዊ ችግር ስለሆነው የኢኮኖሚ ስሌት ምንም የሚነግረን ነገር የለም። እንደ ሙከራ ወይም ፍተሻ አድርገን ማሰባችንስ ተገቢ ነው? በሰው ልጅ ተግባር መስክ እና በኢኮኖሚክስ መስክ ውስጥ ሳይንሳዊ ሙከራ አለ ብዬ አላምንም። በሰው ልጅ ተግባር መስክ ቤተ ሙከራ ማካሄድ አይቻልም ምክንያቱም ሳይንሳዊ ሙከራ በተለያዩ ሁኔታዎች ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸም ወይም በተመሳሳይ ሁኔታ አንድን ምክንያት ብቻ እየቀየሩ መሞከር ይጠይቃል። ለምሳሌ አንድ በካንሰር የተጠቃ እንስሳ የሙከራ መድሃኒት ሲሰጠው ከካንሰሩ ሊፈወስ ይችላል። ይህንን ሙከራ ተመሳሳይ በሽታ በተጠቁ እንሶሶች ላይ በማካሄድ ውጤቱን መፈተሽ ይቻላል። መድሃኒቱን ለአንዳንዶቹ ሰጥቶ ሌሎቹን በመከልከል ውጤት ማነጻጸር ይቻላል። ይህንን አይነት ሙከራ ግን በሰው ልጅ ተግባር መስክ ውስጥ ማካሄድ አይቻልም። በሰው ልጅ ተግባር ውስጥ ቤተ ሙከራዎች የሉም።

የሶቭየት “ሙከራ” ተብሎ የሚጠራው ነገር የሚያሳየው ነገር ቢኖር በመላው አለም የካፒታሊዝም ተምሳሌት ከምትባለው አሜሪካ አንጻር የሶቭየት ሩስያ የኑሮ ደረጃ ለማነጻጸር በሚከብድ ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን ነው።

ይህንን ለሶሻሊዝም ተከታይ ሰው ብትናገር “ነገሮች በሩስያ አስደናቂ ናቸው” የሚል መልስ መስጠቱ አያጠያይቅም። “ነገሮች ምንም አሪፍ ቢሆኑም የሰው የኑሮ ደረጃ በአንጻሩ በጣም ዝቅ ያለ ነው” ልትለው ትችላለህ። ለዚህ ደግሞ “በንጉሰ ነገስት ዘመን ነገሮች ለሩስያውያን ምን ያህል አስከፊ የነበሩ እንደሆነ መርሳት የለብህም። መጥፎ ጦርነትም ስንዋጋ ነበር” በማለት ይመልስልሃል።

ይህ ትክክለኛ ማብራሪያ መሆኑን ወይም አለመሆኑን እዚህ መወያየት አልፈልግም ነገር ግን የሁኔታዎችን ተመሳሳይነት የምትክድ ከሆነ ሙከራ መሆኑንም አብረህ መካድ አለብህ። ይህንንም ተከትለህ እንደሚከተለው ማለት ይኖርብሃል(ይበልጥ ትክክለኛ ስለሆነ)፦ “በተመሳሳይ ግዜ በአሜሪካ ከታየው የተራው ሰው የኑሮ መሻሻል አንጻር የሩስያ ሶሻሊዝም ሊወዳደር የሚችል ለውጥ ይዞ አልመጣም።”

አሜሪካ ውስጥ ስለ አዲስ ነገር ስለ አዲስ ለውጥ ሁሌም(በየሳምንቱ ማለት ይቻላል) መስማት የተለመደ ነው። እነዚህ ለውጦች በንግድ ድርጅቶች ምክንያት የመጡ ናቸው ምክንያቱም በሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ድርጅቶች የሸማቹን ፍላጎት በተሻለ ሁኔታ የሚያሟላ አዲስ ምርትን ወይም ምርትን በዝቅተኛ ዋጋ ጨርሶ ለሸማቹ በወረደ ዋጋ የሚቀርብበትን መንገድ ለማግኘት ቀንና ማታ ይሞክራሉ። ይህንን የሚያደርጉት የሌሎችን ጥቅም ከራሳቸው አስበልጠው አይደለም፤ ይህንን የሚያደርጉት ለራሳቸው ገንዘብ ለማግኘት ነው። ውጤቱ ግን የአሜሪካ የኑሮ ደረጃ በሃምሳ እና በመቶ አመታት ግዜ ውስጥ ከሌሎች ሀገሮች አንጻር ተዓምራዊ ሊባል የሚችል መሻሻል ማሳየቱ ነው። ይህ ስርዓት በሌለበት በሶቭየት ሩስያ ውስጥ ግን ተወዳዳሪ የሚባል ለውጥ ማየት አልተቻለም። ስለዚህ የሶቭየት ስርዓትን ልንከተል ይገባል የሚሉን ሰዎች ክፉኛ ተሳስተዋል።

ሌላም ሊጠቀስ የሚገባው ነገር አለ። የአሜሪካው ሸማች ግለሰብ ሸማችም አለቃም ነው። በአሜሪካ ከአንድ ሱቅ ሲወጡ እንዲህ የሚል ምልክት ሊያነቡ ይችላሉ፦ “ለድጋፍዎ እናመሰግናለን። እባክዎ ተመልሰው ይምጡ።” ነገር ግን በጨቋኝ አምባገነን ስርአት(በዛሬዋ ሩስያ ወይም በሂትለር ጀርመን ስር) ከሚገኝ ሱቅ ሲወጡ ባለሱቁ የሚልዎት ነገር “ይህን ምርት ስለሰጠህ ታላቁን መሪ አመስግን”።

በሶሻሊስት ስርዓት ተመስገን የሚለው አካል ሻጭ ሳይሆን ሸማች ነው። አለቃው ዜጋ ግለሰብ አይደለም። አለቃው ማዕከላዊው ኮሚቴ ወይም ማዕከላዊው ቢሮ ነው። እነዚህ ሶሻሊስት ኮሚቴዎች፣ መሪዎች እና አምባገነኖች የበላይ ናቸው። ቀሪው ሰው የነሱ ታዛዥ ነው።