1ኛው ንግግር፡ ካፒታሊዝም

ካፒታሊዝም

ሰዎች የሚጠቀሟቸው ገላጭ አባባሎች ብዙ ግዜ አሳሳች ናቸው። ሰዎች ስለ ዘመኑ የኢንዱስትሪ እና ንግድ አለቃዎች ሲያወሩ የቸኮሌት ንጉስ ወይም የጥጥ ንጉስ ወይም የመኪና ንጉስ በማለት ይጠሯቸዋል። ሰዎች እነዚህን ስያሜዎች መጠቀማቸው በአሁኑ ዘመን በሚኖሩ የኢንዱስትሪ አለቆች እና በበፊቶቹ የፊውዳል ንጉሶች፣ መሳፍንትታት እና ጌቶች መሃከል መሰረታዊ ልዩነት እንደማይታያቸው ይጠቁማል። ነገር ግን ልዩነቱ እጅግ ትልቅ ነው። ምክንያቱም የቸኮሌት አለቃ በጭራሽ እንደ ገዢ ሀይል ሊቆጠር አይችልም፤ እንደ አገልጋይ እንጂ። ከገበያው ስርአት እና ከሸማቹ ፍላጎት አፈንግጦ በወረረው ግዛት ላይ አይነግስም። የቸኮሌት ንጉስ(ወይም የብረት ንጉስ፣ የመኪና ንጉስ ወይም የማንኛውም ኢንዱስትሪ ንጉስ ሊሆን ይችላል) እጣ ፈንታው በሚሰራበት ኢንዱስትሪ እና በሚያገለግለው ደንበኛ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ንጉስ ንግስናውን ለማስቀጠል በተገዢዎቹ(ሸማቾቹ) መልካም ጸጋ ስር መቆየት ይገባዋል። ከተወዳዳሪዎቹ አንጻር ለሸማቾቹ በቅናሽ ዋጋ የተሻለ አገልግሎት ማቅረብ ያሚያስችለውን አቅም ሲያጣ ንጉሱ ግዛቱን አብሮ ያጣል።

ካፒታሊዝም ከመምጣቱ ከሁለት መቶ አመት በፊት የሰው የማህበረሰብ ደረጃው ከትውልድ እስከ ሞት ቋሚ ነበር። የሰው የማህበረሰብ ደረጃው በዘር ግንድ የተወሰነ እና የማይለወጥ ነበር። በድህነት የተወለደ ሰው ደሃ ሁኖ ይኖራል፣ በሀብት ውስጥ የተወለደ ደግሞ(መሳፍንት ወይም ጌታ) መሳፍንትነቱን እና በመሳፍንትነቱ የሚጎናጸፈውን ንብረት ይዞ እስከ ህይወቱ መጨረሻ ይቀጥላል።

ከምርት ዘርፍ አንጻር በግዜው የነበሩት ኋላቀር የፋብሪካ ኢንዱስትሪዎች ሀብታሙን ማህበረሰብ ብቻ ለማገልገል የቆሙ ነበሩ። አብዛኛው ሰው(የአውሮፓ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ) በግብርናው ዘርፍ ተሰማርቶ ይኖር የነበረ ሲሆን ከተማ ተኮር ከነበረው የፋብሪካ ኢንዱስትሪ ጋር ንክኪ አልነበረውም። ይህ ግትር የፊውዳል ስርአት አድገዋል በሚባሉት የአውሮፓ ክፍሎች ለመቶዎች አመታት አይሎ ቆይቷል።

የካፒታሊዝም ጅማሮ

የገጠሩ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ግን የህዝብ ብዛት መሬቱ ከሚችለው በላይ ተትረፈረፈ። የሚወርሰው ርስትና ንብረት የሌለው ይህ ትርፍ ህዝብ የሚሰራው ስራ አልነበረውም። በከተሞች ነገስታት አማካኝነት ይህ ህዝብ በፋብሪካው ኢንዱስትሪ ስራ እንዳይሰራ ታቅቦ ነበር። ስለዚህ ቁጥሩ እየጨመረ ስለሚሄደው፣ ከማህበረሰብ የተባረረ የማህበረሰብ ክፍል ምን መደረግ እንደነበረበት የሚያውቅ ሰው አልነበረም። እነዚህ ሰዎች “Proletarian”(ወዛደር) በሚለው ቃል ውስጥ ሙሉ መገለጫቸውን የሚያገኙ ሰዎች ነበሩ። መንግስት ከጉልበት ስራ እና ከድህነት ህይወት ውጪ ሌላ አማራጭ ሊሰጣቸው የማይችል በማህበረሰቡ የተተፉ ሰዎች ነበሩ። በአንዳንድ የአውሮፓ ክፍሎች በተለይ በሆላንድ እና በእንግሊዝ የነዚህ ሰዎች ቁጥር ከመብዛቱ የተነሳ የአስራ ስምንተኛውን ክፍለ ዘመን የማህበረሰብ ስርአት ጠብቆ ማቆየት አዳጋች ሁኖ ነበር።

ዛሬ ህንድን እንደመሳሰሉ ተመሳሳይ ሁኔታ እያሳለፉ የሚገኙ ታዳጊ ሀገራት አንስተን ስንወያይ የአስራ ስምንተኛው ክፍለዘመን እንግሊዝ የነበረው ሁኔታ እጅግ ይብስ እንደነበር መርሳት የለብንም። በዛ ግዜ እንግሊዝ 6 ወይም 7 ሚልየን የሚጠጋ የህዝብ ቁጥር ነበራት። ነገር ግን ከዚህ 6 ወይም 7 ሚልየን ከሚሆነው ህዝብ ከሚልየን በላይ(በግምት 2 ሚልየን) የሚሆነው ህዝብ በግዜው የማህበረሰብ ስርአት ምንም አይነት የተመቻቸ ሁኔታ ያልተፈጠረለት በማህበረሰቡ የተተፋ አካል ነበር። ስለዚህ የማህበረሰብ አካል ምን መደረግ አለበት የሚለው ጥያቄ የአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዝ ትልቁ ጥያቄ ነበር።

ሌላ የግዜው ትልቅ ችግር የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ነበር። የታላቋ ብሪታንያ ዜጎች የሚከተለውን ጥያቄ እራሳቸውን በቁም ነገር መጠየቅ ነበረባቸው፦ ለኢንዱስትሪዎቻችን ስራ እና ቤቶቻችንን ለማሞቅ ከምንተማመንባቸው ደኖች ወደፊት እንጨት ማግኘት ሲያቅተን ምን ይውጠናል? ለሀገር ገዢው ክፍል ተስፋ የሚያሳጣ ሁኔታ ነበር። የሀገሩ መሪዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም ነበር፣ እናም እነዚህ ገዢዎች ሁኔታዎችን እንዴት ማሻሻል እንደሚችሉ ምንም ሀሳብ አልነበራቸውም።

ከዚህ ከባድ የማህበረሰባዊ ሁኔታ ነበር የዘመናዊ ካፒታሊዝም ጅማሬዎች ብቅ ያሉት። ከነዚህ ከማህበረሰብ ከተገፉ፣ ከነዚህ ከድሃ ሰዎች መሃል ሰዎችን በማስተባበር ምርት የሚመረትባቸው አነስተኛ ሱቆችን ለማቋቋም የሚጥሩ ሰዎች ነበሩ። ይህ የፈጠራ ስራ ነበር። የነዚህ ፈጣሪዎች ምርት ለላይኛው የማህበረሰብ ክፍል አገልግሎት ብቻ የሚሆን ውድ ምርት አልነበረም፤ ምርቶቹ የሁሉንም ማህበረሰብ ክፍል ፍላጎት የሚያሟሉ ርካሽ ምርቶች ነበሩ። ይህ ዛሬ ለምናውቀው ካፒታሊዝም መነሻ ነበር። የካፒታሊዝም መሰረታዊ መርህ ለሆነው ለጅምላ ምርት መነሻ ነበር። ከዛ በፊት የነበሩት የምርት ኢንዱስትሪዎች የላይኛውን የማህበረሰብ ክፍል ፍላጎት ብቻ ለሟሟላት የተተቋቋሙ በመሆናቸው አገልግሎታቸው ከተማ ለሚኖረው ህዝብ ብቻ የነበረ ሲሆን አዲሶቹ የካፒታሊስት ኢንዱስትሪዎች ግን በአንጻሩ በሰፊው ህዝብ የሚሸመቱ ምርቶችን ማምረት ችለዋል። የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት ለማሟላት የሚደረግ ጅምላ ምርት ነበር።

ዛሬ በከፍተኛ ደረጃ የዳበረ የጅምላ ምርት ስርአት ያላቸው ሀገራት ሁሉ መሰረታዊ የካፒታሊዝም መርሃቸው ይህ ነው። በግራኝ ርዕዮተ ዓለም ተከታዮች የከረረ የቃል ጥቃት ኢላማ የሆኑት የዛሬዎቹ ግዙፍ የንግድ ተቋማት በምርቶቻቸው የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት ነጥለው ለማሟላት የቆሙ ናቸው። ለባለሃብት አገልግሎት ብቻ የሚውል የቅንጦት ምርት የሚያመርቱ ድርጅቶች ግዙፍ የሚያስብላቸው የተቋም ታላቅነት ላይ ሊደርሱ አይችሉም። ዛሬ ደግሞ የታላቅ ፋብሪካ ዋና ደንበኞች የራሱ ፋብሪካ ሰራተኞች ናቸው። በካፒታሊዝም የምርት መርህ እና በቀድሞው ዘመን በነበረው የፊውዳሊዝም ምርት መርህ መሃከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት ይህ ነው።

የንግድ ድርጅቶች ደንበኛን ያገለግላሉ

ግዙፍ የንግድ ድርጅቶችን አስመልክቶ በአምራቹ እና በሸማቹ ሀይል መሃል ስላለው ትልቅ ልዩነት ሰዎች ሲያወሩ ፍጹም ተሳስተዋል። አሜሪካ በሚገኙ ግዙፍ የምርት ማከፋፈያ መደብሮች ውስጥ “ደንበኛው ሁሌም ትክክል ነው” የሚለውን መፈክር መስማት የተለመደ ነው። በመደብሩ ለሽያጭ የሚቀርቡትን ምርቶች የሚያመርተው ሰው ግን እራሱ ሸማቹ ነው። ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች ከፍተኛ ስልጣን እና አቅም እንዳላቸው የሚያስቡም ሰዎች ቢሆኑ የተሳሳቱ ናቸው፤ ምክንያቱም የነዚህ ትላልቅ ድርጅቶች ቀጣይነት ሙሉ በሙሉ የሚወሰነው ምርቶቻቸውን በሚሸምቱት ደንበኞች ነው። ታላቅ የሚባለው ድርጅት እንኳ ደንበኞቹን ሲያጣ የተቆናጠጠውን ስልጣን እና ተጽእኖ ፈጣሪነት አብሮ ያጣል።

ከሃምሳ ወይም ከስልሳ አመት በፊት የባቡር ድርጅቶች በሁሉም የካፒታሊስት ሀገሮች የደረሱበት ግዝፈት እና የተቀዳጁት ስልጣን ከልክ ያለፈ እንደሆነ በሰፊው ይወራ ነበር፤ ሞኖፖል እንደነበራቸው እና ከነሱ ጋር መወዳደር ከንቱ እንደሆነ ይነገር ነበር። በትራንስፖርት ዘርፍ ካፒታሊዝም ተወዳዳሪዎችን በማጥፋት እራሱን ወደገደለበት ደረጃ እንደደረሰ ይገለጽ ነበር። በግዜው ሰዎች ልብ ያላሉት ነገር ግን የባቡሮቹ አቅም የተመሰረተው ሰዎችን ከየትኛውም የመጓጓዣ ዘዴ በተሻለ ሁኔታ በማገልገላቸው መሆኑን ነው። በእርግጥ ከነዚህ ግዙፍ የባቡር ድርጅቶች ጋር ለመወዳደር ሲባል ከነሱ መስመር ትይዩ የሆነ ሃዲድ መስራት ሞኝነት ነው ምክንያቱም የበፊቱ ሃዲድ የመስመሩን ፍላጎት የሚያሟላ በመሆኑ። ነገር ግን በአጭር ግዜ ውስጥ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ብቅ አሉ። የውድድር ነጻነት ማለት የሌሎችን ስራ አመሳስሎ ወይም ገልብጦ በመስራት ብቻ ስኬታማ መሆን ይቻላል ማለት አይደለም። የጋዜጣ ነጻነት ማለት የራስ የሆነ አዲስ ጽሁፍ የመጻፍ መብት ማለት እንጂ ሌላ ሰው የጻፈውን ጽሁፍ ገልብጦ የማተም መብት ማለት አይደለም፤ ግልባጭ አትሞ የመጀመርያውን ጸሃፊ ስኬት የማጣጣም መብት ማለት አይደለም። የውድድር ነጻነት በውድድር አማካኝነት የባቡር ድርጅቶችን ንግድ ስጋት ውስጥ ሊያስጥል የሚችል አዲስ ስራ ወይም ፈጠራ የመስራት መብትን ያጎናጽፋል።

ተሳፋሪን በማጓጓዝ ስራ በአሜሪካ ውስጥ የባቡር ተወዳዳሪ የሆኑት አውቶብሶች፣ የቤት እና ጭነት መኪኖች፣ እንዲሁም አውሮፕላኖች የባቡሮቹን ኪስ ከመጉዳት አልፈው ሙሉ በሙሉ ለማሸነፍ ጫፍ ደርሰዋል።

የካፒታሊዝም መጎልበት ፋይዳው ሰው ሁሉ ደንበኛውን በተሻለ ሁኔታ እና በተሻለ ዋጋ የማገልገል መብት እንዲኖረው ማድረጉ ነው። ይህ መንገድ፤ ይህ መርህ አጭር በሚባል ግዜ ውስጥ አለምን መቀየር ችሏል። አለም የህዝብ ቁጥሯን ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ እንድትጨምር አስችሏታል።

በአስራስምንተኛው ክፍለዘመን የእንግሊዝ ሀገር መሬት መሸከም የሚችለው 6 ሚልየን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ሰዎችን ነበር። ዛሬ በእንግሊዝ ከሃምሳ ሚልየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከአስራስምንተኛው ክፍለ ዘመን ባለሃብቶች በሚልቅ የኑሮ ደረጃ ህይወታቸውን ይመራሉ። የብሪታንያ ህዝብ ሃይል በቀላሉ ሊታለፉ በሚችሉ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ክስተቶች ባይጠመድ ኖሮ የሰው የኑሮ ደረጃ አሁን ከሚታየው የኑሮ ደረጃ እጅግ በበለጠ ነበር።

የካፒታሊዝም እውነታዎች ከላይ የተጠቀሱት ናቸው። ስለዚህ አንድ እንግሊዛዊ(ለነገሩ የየትኛውም ሀገር ዜጋ ሊሆን ይችላል) ካፒታሊዝምን እቃወማለሁ ብሎ ለጓደኞቹ ሲያወራ እንዲህ ብሎ ጥሩ መልስ መስጠት ይቻላል። “የዚህ አለም የህዝብ ብዛት ካፒታሊዝም በፊት ከነበረው በአስር እጥፍ እንደጨመረ ታውቃለህን? ዛሬ ሁሉም ሰው በቅድመ ካፒታሊዝም ይኖሩ ከነበሩት ቅድመ አያቶቹ የተሻለ የኑሮ ደረጃ እንዳለው ታቃለህን? ካፒታሊዝም ባይኖር ከማይወለዱት ከአስሩ ዘጠኝ ሰዎች አንዱ አለመሆንህን በምን እርግጠኛ ሆንክ? ለህይወትህ የምትሰጠው ግምት አነሰም በለጠም ዛሬ በህይወት መገኘትህ ለካፒታሊዝም ስኬት ምስክር ነው።”

ምንም እንኳ ብዙ ጥቅም የሰጠን ቢሆንም በካፒታሊዝም ላይ ቁጣ አዘል ትችት እና ኩነና ይቀርብበታል። የዚህን ጥላጫ መንስኤ መረዳት አስፈላጊ ነው። የካፒታሊዝም ጥላቻ መጀመርያ የተነሳው ከሰፊው ህዝብ ወይም ከወዛደሩ ክፍል ሳይሆን ከእንግሊዝ እና ከአውሮፓ የመሬት ባላባቶች፣ ክቡራን እና መኳንንቶች መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው። እነዚህ የማህበረሰብ አባላት ካፒታሊዝምን ላመጣባቸው መዘዝ ተጠያቂ አደረጉት። በአስራዘጠነኛው ክፍለዘመን ጅማሮ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሰራተኞቹ ይከፍል የነበረው ከፍ ያለ ደመዎዝ የመሬት ክቡራን ለእርሻ ሰራተኞቻቸው በእኩል ደረጃ ደመዎዝ ከፍ እንዲያደርጉ አስገድዷቸው ነበር። በዚህም ሳብያ የኢንዱስትሪ ሰራተኞች በሚኖሩበት የዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በማመካኘት ባለሃብቶቹ ኢንዱስትሪዎቹን መተቸት ጀመሩ።

ካፒታሊዝም የማህበረስቡን የኑሮ ደረጃ ከፍ ያደርጋል

በእርግጥ ከኛ የኑሮ ደረጃ አንጻር የየዛኔ ሰራተኞች የኑሮ ደረጃ ከሚገባ በላይ ዝቅተኛ ነው። በካፒታሊዝም ቀዳሚ ቀናት ሁኔታዎች ፍጹም አስደንጋጭ የነበሩ ቢሆንም የዚህ መንስኤ ግን አዲስ የተቋቋሙት የካፒታሊዝም ኢንዱስትሪዎች ሰራተኞቻቸውን መበደላቸው አይደለም። አዲሶቹ የፋብሪካ ሰራተኞች ከቅጥር በፊት የነበራቸው የኑሮ ደረጃ ከሰብአዊነት ዝቅ ያለ የሚባል ነበር።

እነዚህ ፋብሪካዎች ሴቶች እና ልጆችን አጥጋቢ ከሚባል የኑሮ ዘይቤ አፈናቅለው የፋብሪካ ሰራተኛ ማድረጋቸው ደጋግሞ የሚወራ ዝነኛ አፈታሪክ ቢሆንም ታሪክ ከመዘገባቸው ግዙፍ ውሸቶች አንዱ ነው። ፋብሪካ የሚሰሩት እናቶች ምግብ የሚያበስሉበት እቃ እንኳ አልነበራቸውም። እንደሚባለው ወደ ፋብሪካ የሄዱት ቤታቸውን እና ኩሽናቸውን ጥለው ሳይሆን ኩሽና ስላልነበራቸው ወይም ኩሽና የነበራቸውም ቢሆኑ በኩሽናቸው የሚያበስሉት ምግብ እና የሚጠጡት ውሃ ያልነበራቸው በመሆኑ ነው። ልጆቹ ደግሞ ከተመቻቹ መዋእለ ሕፃናት የወጡ አልነበሩም። እየተራቡ እና እየሞቱ ነበር። ለዚህ አስከፊ የኑሮ ሁኔታ የካፒታሊዝምን ጅማሮ እንደ መንስኤ የሚያነሱ ትርክቶች በዚህ አንድ እውነታ ይረታሉ። የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን በሚባሉት በነዚህ የብሪታንያ ካፒታሊዝም ጅማሬ በነበሩት አመታት(እ.አ.አ ከ1760-1830) የእንግሊዝ የህዝብ ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል። ይህ ማለት በበፊቱ ዘመናት ግዜ ሳያድጉ ይሞቱ የነበሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች አድገው አዋቂ እድሜ መድረስ ችለዋል።

የበፊቱ ዘመን የኑሮ ሁኔታ አጥጋቢ አለመሆኑ አያጠያይቅም። ኑሮን ያሻሻለው ግን የካፒታሊስት ንግድ ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ(ምርቶችን ውጭ ሀገር ልኮ ምግብ እና ጥሬ እቃ በማስገባት) የሰራተኞቻቸውን የኑሮ ፍላጎት ማሟላት የቻሉት እነዛ ቀዳሚ ኢንዱስትሪዎች ናቸው። የካፒታሊዝም የመጀመርያዎቹ የታሪክ ጸሃፊዎች ደጋግመው ሃሰተኛ ታሪክ(ለዘብ ያለ ቃል መጠቀም አስቸጋሪ ነው) አስቀምጠው አልፈዋል።

እንደ ማስታወሻ ይናገሯት የነበረች አንድ ታሪክ(ፈጥረዋትም ሊሆን ይችላል) ቤንጃሚን ፍራንክሊንን ይመለከታል። እንደ ታሪኩ ከሆነ ቤን ፍራንክሊን እንግሊዝ ውስጥ የሚገኝ የጥጥ ፋብሪካን ለመጎብኘት በሄደበት ግዜ የፋብሪካው ባለቤት በኩራት ተሞልቶ “እዚህ የምታየው ሀንጋሪ የምንልካቸውን የጥጥ ምርቶች ነው” ይለዋል። ቤን ፍራንክሊን አካባቢውን ዞር ብሎ በመቃኘት የሰራተኞቹን የማይረባ አለባበስ ካስተዋለ በኋላ እንዲህ ሲል ይመልሳል “ለሰራተኞችህስ የሚሆን ነገር ለምን አታመርትም”?

ነገር ግን በፋብሪካው ባለቤት የተነሳው የዛ የውጭ ንግድ ፋይዳ በተዘዋዋሪ መንገድ ቢሆንም የፋብሪካው ምርት የሰራተኞቹን ፍላጎት ለማሟላት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይጠቁማል ምክንያቱም እንግሊዝ ጥሬ እቃዎችዋን ሁሉ ከውጭ አስመጪ በመሆኗ ነው። በእንግሊዝ ውስጥም ሆነ በአውሮፓ አህጉር የሚበቅል ጥጥ አልነበረም። የምግብም እጥረት በእንግሊዝ በመከሰቱ በግዜው ከፖላንድ፣ ሩስያ እና ሀንጋሪ ምግብ መግባት ነበረበት። እነዚህ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ወደ ሃገር ውስጥ ለሚገቡት የምግብ ምርቶች ክፍያ የነበሩ ሲሆን ይህ ከውጭ የገባው የምግብ ምርት የብሪታንያን ህዝብ ህይወት መታደግ የቻለ ነበር። በግዜው የተጻፉ ታሪኮችን በመጥቀስ የግዜው ክቡራን እና ባላባቶች በሰራተኛው ክፍል ላይ ስለነበራቸው አመለካከት ብዙ ምሳሌ መስጠት ይቻላል። ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ መጥቀስ እፈልጋለሁ። አንዱ ስለ ታዋቂው የብሪታንያ “Speenhamland”(ስፒንሃምላንድ) ስርአት ይመለከታል። በዚህ ስርአት የብሪታንያ መንግስት በህግ ካስቀመጠው የደመዎዝ ወለል በታች ሰራተኞቻቸውን ለሚከፍሉ ድርጅቶች መንግስት በወለሉ እና በደመዎዙ መሀል ያለውን ልዩነት ይከፍል ነበር። ይህ ስርአት የመሬት ባላባቶች ሰራተኞቻቸውን ከፍ ያለ ደመዎዝ እንዳይከፍሉ የታደገ ስርአት ነበር። እነዚህ ክቡራን የተለመደውን ዝቅተኛ የግብርና ደመዎዝ በመክፈል ይቀጥላሉ፣ መንግስት ማሟያውን ይከፍላል፣ ሰራተኞቹም ገጠሩን ለቀው ከተማ የፋብሪካ ስራ ፍለጋ ከመሄድ ይታቀባሉ።

ከሰማንያ አመት በኋላ ካፒታሊዝም ከእንግሊዝ ተነስቶ በተስፋፋባት በአውሮፓ አህጉር የመሬት ባላባቶች በተመሳሳይ ሁኔታ አዲሱን የምርት ስርአት ሲቃወሙ ይታያሉ። በጀርመን ግዛት የተሻለ ደመዎዝ ለሚከፍሉት ካፒታሊስት ኢንዱስትሪዎች ሰራተኞቻቸውን በብዛት ያጡት የፕሩሺያ መኳንንቶች ለዚህ ችግር የተለየ ስያሜ ሰተውታል፡- “ከገጠር በረራ”(Landflucht)። በመኳንንቶቹ እይታ አስከፊ ስለነበረው ስለዚህ ሁኔታ ምን መደረግ አለበት የሚል ውይይት በጀርመን ፓርላማ ተካሂዷል።

ታዋቂው የጀርመን ግዛት ቻንስለር ልዑል ቢዝማርክ አንድ ቀን እንዲህ ሲል ንግግር ያደርጋል፦ “የኔ ንብረት ላይ ይሰራ የነበረን አንድ ሰው በርሊን ውስጥ አግኝቸው እንዲህ ስል ጠየኩት ‘ለምንድን ነው መሬቴን ለቀህ የሄድከው? ገጠሩን ለቀህ ለምን ሄድክ? አሁን በርሊን የምትኖርበት ምክንያት ምንድን ነው?’” በቢዝማርክ አገላለጽ ሰውየው እንዲህ ሲል ይመልስለታል፦”እዚህ በርሊን የምታገኛቸው አይነት የአትክልት ስፍራዎች(ተቀምጠህ ቢራ የምትጠጣባቸው እና ሙዚቃ የምታዳምጥባቸው ስፍራዎች) ያንተ መሬት ላይ የሉም።” በእርግጥ ይህ ታሪክ ከቀጣሪው ቢዝማርክ እይታ የተነገረ ነው። የሰራተኞቹ እይታ ግን ይህ አልነበረም። ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሄዱበት ምክንያት ኢንዱስትሪዎች የተሻለ ደመዎዝ ከፋይ በመሆናቸው እና የሰራተኞቻቸውን የኑሮ ደረጃ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ማሻሻል በመቻላቸው ነው።

ዛሬ በካፒታሊስት ሀገሮች ውስጥ በከፍተኛ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በሚኖሩ የማህበረሰብ አካላት መሃከል በንጽጽር እዚህ ግባ የሚባል የኑሮ ልዩነት የለም። ሁለቱም የማህበረሰብ ክፍሎች ምግብ፣ ልብስ እና መጠለያ አይቸገሩም። ነገር ግን በአስራ ስምንተኛው ክፍለዘመን እና ከዛ አስቀድሞ በነበረው ግዜ በመሃከለኛ ገቢ ደረጃ በሚኖር ሰው እና በዝቅተኛ ገቢ ደረጃ በሚኖር ሰው መሃከል የነበረው ልዩነት ባለጫማ የመሆን እና ያለመሆን ነበር። በዛሬው አሜሪካ በሃብታም እና በድሃ ሰው መሃል ያለው ልዩነት የካዲላክ መኪና የመንዳት ወይም የሼቭሮሌት መኪና የመንዳት ልዩነት ነው። የሼቭሮሌት መኪናው ያገለገለ ቢሆን እንኳ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ ከሌላው መኪና አንጻር ለባለቤቱ ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣል። ከሃምሳ በመቶ በላይ የሚሆኑ የአሜሪካ ነዋሪዎችም እራሳቸው ባለቤት በሆኑበት ቤት ወይም አፓርታማ ውስጥ ነው የምሚኖሩት።

ካፒታሊዝም ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች መነሻ የሰራተኛው ክፍል ደመዎዝ የሚመዘዘው ከእዛው ከሰራተኛው ማህበረሰብ ሳይሆን ከሌላ አካል እንደመጣ አድርጎ ከሚያስብ የተሳሳት አመለካከት ነው። ኢኮኖሚስቶች እና የኢኮኖሚክ ንድፈ ሃሳብ ተማሪዎች ሰራተኛን እና ሸማችን ለይተው ማስቀመጣቸው ተገቢ ቢሆንም እውነታው ግን ሁሉም ሸማች በዚህም ሆነ በዚያ ሊያወጣው ያሰበውን ገንዘብ መጀመርያ ገቢ ማድረግ አለበት። እናም ከዚህ ሸማች ማህበረሰብ እጅግ በጣም ብዙ የሚሆኑት ሰዎች ከራሱ ከምርት አምራቹ ማህበረሰብ የተውጣጡ ናቸው። በካፒታሊዝም ስር የደመዎዝ መጠን የሚወሰነው ደመዎዝ ተከፋይ ከሆነው ማህበረሰብ ውጭ በሆነ በሌላ አካል አይደለም። የደመዎዝ መጠን የሚወሰነው በእራሱ በደመዎዝ ተከፋዩ ማህበረሰብ ነው። የፊልም ተዋናዩን ደመዎዝ የሚከፍለው የሆሊውድ ፊልም ድርጅት አይደለም፤ ፊልሙን ለማየት ገንዘቡን የሚከፍለው ማህበረሰብ እንጂ። ቦክሰኞች ከቦክስ ግጥሚያ የሚያገኙትን ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፍላቸው የግጥሚያው አዘጋጅ ስራ ፈጣሪ አይደለም፤ ግጥሚያውን ለመመልከት ገንዘብ የሚከፍለው ታዳሚ እንጂ። በኢኮኖሚክ ንድፈ ሃሳብ ውይይት ውስጥ ቀጣሪ እና ተቀጣሪ ተለይተው ቢቀመጡም ይህ ልዩነት ጠለቅ ያለውን እውነታ አያንጸባርቅም፤ እውነታው ቀጣሪው እና ተቀጣሪው በመጨረሻ እይታ ተመሳሳይ ሰዎች ናቸው።

የብዙ ልጆች ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆነ ሰው በብቸኝነት እየኖረ እራሱን ብቻ ከሚያስተዳድር ሰው ጋር እኩል ተከፋይ ሆኖ ሲገኝ በተለያዩ ሀገራት ሁኔታው ኢ-ፍትሃዊ ነው የሚያስብላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ስራ ቀጣሪ የደመዎዝ መጠንን ሲወስን የቅጥረኛውን የቤተሰብ ቁጥር ግምት ውስጥ ባስገባ መልክ ይሁን ወይ የሚለው ጥያቄ የተሳሳተ ጥያቄ ነው።

በዚህ ሁኔታ እራሳችንን መጠየቅ ያለብን ጥያቄ እንደሚከተለው ነው፦ አንተ እንደ ግለሰብ ምርት ከመግዛትህ በፊት(የዳቦ ቁራሽ ሊሆን ይችላል) ዳቦውን ያመረተው ሰው 6 ልጅ እንደሚያስተዳድር ብታውቅ ተጨማሪ ለመክፈል ዝግጁ ነህ? ሀቀኛ ሰው እንደሚከተለው ለዘብ ባለ መልኩ ቢናገርም አሉታዊ መልስ ከመስጠት አይቆጠብም “በመርህ ደረጃ አደርጋለሁ ብል ደስ ይለኛል። እውነታው ግን ዋጋ ከቀነሰልኝ ምንም ልጅ ከሌለው ዳቦ አምራች መግዛትን እመርጣለሁ።” እውነታው አምራች ሰራተኞቹን ለመክፈል የሚያስችለውን ገቢ ከሸማቾች ክፍያ ማግኘት ካልቻለ በንግድ መቀጠል አይችልም።

የካፒታሊዝም ስርአት “ካፒታሊዝም” የሚለውን ስያሜ ያገኘው ለስርአቱ ጓደኛ በሆነ ሰው ሳይሆን በታሪክ ከተመዘገቡ ስርአቶች ሁሉ መጥፎ እና በሰው ልጅ ላይ ከደረሱ ትልቅ ክፋቶች አንዱ ነው ብሎ በሚያስብ ሰው ነው። ይህ ሰው ካርል ማርክስ ነው። ይህ ቢሆንም ግን ይህንን ምክንያት በማድረግ ማርክስ የተጠቀመውን ቃል ገሸሽ ማድረግ ተገቢ አይደለም ምክንያቱም ካፒታሊዝም የሚለው ቃል ካፒታሊዝም ያስከተለውን ታላቅ አዎንታዊ የማህበረሰባዊ ለውጦች መነሻ በውስጡ የያዘ ቃል ነው። የነዚህ ለውጦች መንስኤ የካፒታል ክምችት ነው። የነዚህ ለውጦች መሰረት ሰዎች የሚያገኙትን ገንዘብ በሙሉ ከማጥፋት ይልቅ የተወሰነውን መቆጠባቸው እና መዋዕለ ንዋይ ላይ ማፍሰሳቸው ነው። ይህ ብዙ የግንዛቤ ስህተት ያለው ችግር ሲሆን እዚህ በማደርጋቸው ንግግሮች ሰዎች በካፒታል ክምችት፣ በካፒታል አጠቃቀም እና ይህ አጠቃቀም ስለሚሰጣቸው ሁለንተናዊ ጥቅሞች ዙርያ የሚያነሷቸውን መሰረታዊ የግንዛቤ ስህተቶች የማጽዳት እድል ይኖረኛል። ስለ ውጭ ኢንቨስትመንት እና የግዜው የፖለቲካ ችግር ስለሆነው ኢንፍሌሽን አስመልክቼ በማደርጋቸው ንግግሮች ስለ ካፒታሊዝም ነጥዬ አነሳለሁ። እንደምታውቁት ኢንፍሌሽን እዚህ ሀገር ብቻ የተፈጠረ ችግር ሳይሆን በአለም ዙርያ ያለ ችግር ነው።

ካፒታሊስት ቁጠባ ሰራተኞችን ይጠቅማል

ስለ ካፒታሊዝም ብዙ ግዜ የማይስተዋለው እውነታ ይህ ነው፦ ቁጠባ ማለት ለአምራቹም ሆነ ለደመዎዝተኛው ጥቅም ማለት ነው። የተወሰነ ገንዘብ የቆጠበ ሰው(አንድ ሺህ ብር እንበል) ገንዘቡን ወጪ ከማድረግ ይልቅ በቁጠባ ሂሳብ ወይም በኢንሹራንስ ድርጅት ውስጥ ሲያስቀምጥ ገንዘቡ ወደ ስራ ፈጣሪ ወይም ነጋዴ እጅ ይገባል ማለት ነው። ይህ ስራ ፈጣሪ ትላንት በቂ ካፒታል ባለመኖሩ ሊጀምረው ያልቻለውን ፕሮጀክት በዚህ ገንዘብ መጀመር ይችላል።

ይህ ነጋዴ በዚህ ተጨማሪ ካፒታል ምን ያደርጋል? መጀመርያ ማድረግ ያለበት ነገር ካፒታሉን ተጠቅሞ አዲስ ሰራተኞችን መቅጠር እና ጥሬ እቃዎችን መግዛት ነው። ይህ በሚሆንበት ግዜ በገበያው ለሰራተኞች እና ለጥሬ እቃዎች የሚንጸባረቀው ፍላጎት(ዲማንድ) ይጨምራል። ይህ ለውጥ ደግሞ በተራው የሰራተኞች ደሞዝ እንዲጨምር እና የጥሬ እቃዎች ዋጋ እንዲወደድ ያደርጋል። ቆጣቢው አካል ወይም ስራ ፈጣሪው ትርፍ ከማግኘቱ ከረጅም ግዜ በፊት ስራ አጥ የነበረው አዲስ ቅጥረኛ፣ የጥሬ እቃ አምራቹ፣ ገበሬው እና ተቀጣሪው ሃይል የአዲሱ ቁጠባ ጥቅም ተቋዳሽ ናቸው።

ስራ ፈጣሪው ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ መሆኑ የሚወሰነው በገበያው የወደፊት ሁኔታ እና ስራ ፈጣሪው በነገ ገበያ አዋጭነት ላይ ባደረገው የትንበያ ትክክለኝነት ነው። ሰራተኞች እና የጥሬ እቃ አምራቾች ግን ሁሌም ቀዳሚ ተጠቃሚዎች ናቸው። ከሰላሳ እና ከአርባ አመት በፊት በማንጓጠጥ “የደሞዝ ፖሊሲ” ተብሎ ስለሚጠራው የሄንሪ ፎርድ የደመዎዝ ስርአት ብዙ ነገር ተብሎ ነበር። ከአቶ ፎርድ ግዙፍ ስኬቶች መሃል አንዱ ከሌሎች ባለኢንዱስትሪዎች እና ባለፋብሪካዎች ጋር ሲነጻጸር ለሰራተኞቹ ከፍ ያለ ደመዎዝ መክፈሉ ነው። ይህ የደመዎዝ መጠን በአቶ ፎርድ ተቺዎች የፈጠራ ደመዎዝ ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን ይህ የፈጠራ ደመዎዝ የአቶ ፎርድ የነጻነት ገጽታ ውጤት ነበር። ቀድመው የተቋቋሙ ንግዶች በሚሰሩበት ስፍራ ተወዳዳሪ መሆን የሚፈልግ አዲስ የንግድ ወይም የፋብሪካ ቅርንጫፍ ሰራተኞችን ከሌላ የስራ ስምሪቶች፣ ከሌሎች የሀገር ክፍሎች፣ ከሌሎች ሀገራትም ጭምር መሳብ መቻል አለበት። ይህን ለማድረግ ብቸኛው መንገድ ሰራተኞችን ለስራቸው የተሻለ ደመዎዝ መስጠት ነው። በካፒታሊዝም የቀደምት ቀናትም ሆነ ዛሬ እየተከናወነ ያለው ነገር ይህ ነው።

የታላቋ ብሪታንያ የጥጥ ምርት አምራቾች ምርት በጀመሩበት ግዜ ሰራተኞቻቸውን ከበፊት ደመዎዛቸው የተሻለ ደመዎዝ ይከፍሉ ነበር። በእርግጥ ከነዚህ ሰራተኞች አብዛኞቹ ከዛ በፊት ደመዎዝተኛ ያልነበሩ በመሆናቸው የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ደመዎዝ ለመቀበል ዝግጁ ነበሩ። ከአጭር ግዜ በኋላ ግን የካፒታል ክምችት እና የሚመሰረቱ ድርጅቶች ብዛት እየጨመረ በሄደበት ሁኔታ የደመዎዝ መጠን አብሮ ከፍ እያለ በመሄዱ ቅድም እንደጠቀስኩት የብሪታንያ የህዝብ ብዛት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መጨመር ችሏል።

ሃብታሙን ይበልጥ ሃብታም እና ድሃውን ይበልጥ ድሃ እያደረገ ይሄዳል ተብሎ በአንዳንድ ሰዎች ካፒታሊዝም በንቀት የሚገለጽበት መንገድ ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው በስህተት የተሞላ ነው። የሶሻሊዝምን መምጣት የተነበየው የማርክስ ጽሁፍ መሰረቱ ሰራተኛው በግዜ ሂደት ይበልጥ እየደሀየ፣ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ይበልጥ እየማቀቀ በመጨረሻም የሀገሩ ሀብት በተወሰኑ ሰዎች ወይም በአንድ ሰው እጅ ይከማቻል የሚል መላምት ነው። ከዚያም ድሃ የተደረገው ሰፊው የሰራተኛ ማህበረሰብ መጨረሻ ላይ በማመጽ የባለሃብቱን ሃብት ይነጥቃል። ነገሮች እንደ ካርል ማርክስ አስተሳሰብ ቢሆኑ በካፒታሊስት ስርአት የሰራተኛው ኑሮ የሚሻሻልበት ምንም አይነት እድልም ሆነ መንገድ አይኖርም።

እ.አ.አ በ1864 ማርክስ በአለም አቀፍ ሰራተኞች ማህበር ፊት ቀርቦ ባደረገው ንግግር የሰራተኛ ማህበራት የሰራተኛውን የኑሮ ሁኔታ የማሻሻል አቅም አላቸው የሚለው አስተሳሰብ ፍጹም ስህተት እንደሆነ ተናግሯል። የሰራተኛ ማህበራት ፖሊሲ የሆኑት የደመዎዝ ጭማሪ እና የስራ ሰአት ቅነሳ ጥያቄዎች ወግ አጥባቂ ፖሊሲዎች ናቸው ያለ ሲሆን ወግ አጥባቂ(ኮንሰርቫቲቭ) የሚለው ቃል ማርክስ ሊጠቀማቸው ከሚችላቸው አውጋዥ ቃላት ዋነኛው ነበር። ሰራተኛ ማህበራት አዲስ እና አብዮታዊ ይዘት ያለው ግብ እንዲያነግቡ ጠቆመ። ሰራተኛ ማህበራት የደሞዝ ስርአትን ሙሉ በሙሉ እንዲያስወግዱ እና የግለሰብ የምርት ይዞታ ስርአትን መንግስት የምርት ተቋማትን በሚቆጣጠርበት በሶሻሊዝም ስርአት እንዲተኩ አሳሰበ።

የአለምን ታሪክ በተለይ ደግሞ እ.አ.አ ከ1865 ዓ.ም በኋላ ያለውን የእንግሊዝ ታሪክ በምናይበት ግዜ ማርክስ በሁሉም ረገድ እንደተሳሳተ እንገነዘባለን። በምዕራቡ አለም ከሚገኙ ካፒታሊስት ሀገሮች ውስጥ የህዝብ የኑሮ ደረጃ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ያልተቀየረበት ሀገር የለም። በነዚህ ባለፉት ሰማንያ እና ዘጠና አመታት የተመዘገቡት ለውጦች የካርል ማርክስን ትንበያዎች የሚጻረሩ ናቸው። የማርክስ ፈለግ ተከታይ የሆኑት ሶሻሊስቶች የሰራተኛው የኑሮ ደረጃ በምንም መልኩ ሊሻሻል አይችልም ብለው ያምኑ ነበር። በግዜው እውቅና ያፈራውን “የደመዎዝ ብረት ህግ” ብለው የሰየሙትን የተሳሳተ ንድፈ ሃሳብ ይከተሉ ነበር። ይህ ህግ በካፒታሊዝም ስርአት ውስጥ የሰራተኛው ደመዎዝ ህይወት ለመምራት የሚያበቃ ደረጃ ሊደርስ እንደማይችል ይደነግጋል።

ማርክሲስቶቹ ንድፈ ሀሳባቸውን የቀመሩት በዚህ መልኩ ነው፦ የሰራተኛ ደመዎዝ ኑሮን ለማሸነፍ በሚያስችል ደረጃ ቢጨምር እንኳ ሰራተኛው ተጨማሪ ልጅ ይወልዳል። እነዚህ ልጆች ደግሞ አድገው ወደ ስራ ገበያ ሲገቡ በገበያው የሚወዳደረውን የሰራተኛ ብዛት እንዲጨምር በማድረግ የደመዎዝ መጠን እንዲቀንስ ይዳርጋሉ። በዚህ ሁኔታ የሰራተኛው ደመዎዝ መልሶ በመውረድ ኑሮን ለማሸነፍ ከሚያስፈልገው መጠን በታች ወይም ከሞት ብቻ የሚያስጥል አይነት ደመዎዝ ይሆናል። ነገር ግን ይህ የማርክስ እና የሌሎች በርካታ ሶሻሊስቶች አስተሳሰብ የሰራተኛውን ማህበረሰብ የሚያይበት አይን የስነ ህይወት ተመራማሪዎች እንስሶችን ከሚያጠኑበት አይን የሚለይ አይደለም። ለምሳሌ የአይጦችን።

እንስሶች ወይም ረቂቅ ተሕዋሲያን የሚመገቡት የምግብ መጠን ሲጨመር በህይወት የሚቆዩት የእንስሶች ብዛት አብሮ ይጨምራል። የምግብ መጠናቸው ሲቀነስ ደግሞ ብዛታቸው አብሮ ይቀንሳል። የሰው ልጅ ግን ይለያል። ማርክሲስቶች እውቅና ባይሰጡትም ቅጥረኛው ማህበረሰብ ከመመገብ እና ቁጥሩን ከማብዛት ውጭ ሌሎች ፍላጎቶች አሉት። የደመዎዝ ጭማሪ ፋይዳው የህዝብ ብዛት እንዲጨምር ማድረግ ብቻ ሳይሆን በዋነኝነት የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ከፍ እንዲል ማድረግ ነው። ለዛ ነው ዛሬ በአሜሪካ እና በምዕራቡ አለም በአፍሪካ ከሚገኙ የታዳጊ ሀገራት አንጻር የተሻለ የኑሮ ደረጃ ያለው።

መገንዘብ ያለብን ዋናው ነገር ይህ ከፍ ያለ የኑሮ ደረጃ በካፒታል አቅርቦት ላይ የተመሰረተ ነው። አሜሪካ በሚታየው የኑሮ ሁኔታ እና በህንድ በሚታየው የኑሮ ሁኔታ መሃከል ያለው ዋና ልዩነት እዚህ ላይ ነው። ተላላፊ በሽታዎችን የምንዋጋባቸው ዘመናዊ መንገዶች በህንድ ሀገር በተወሰነ ደረጃ በመስፋፋታቸው የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ቢችልም ይህ ጭማሪ ከካፒታል መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ጭማሪ ጋር አብሮ የተመዘገበ ባለመሆኑ የሀገሩ የድህነት መጠን አብሮ ጨምሯል። የአንድ ሀገር የብልጽግና ከፍታ በነፍስ ወከፍ ከሚፈሰው የካፒታል መዋዕለ ነዋይ ፍሰት ጋር ተመጣጣኝ ነው።

በቀጣዮቹ ንግግሮቼ ስለነዚህ ችግሮች በስፋት የመዳሰስ እና የማብራራት እድሉ ይኖረኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደ “በነፍስ ወከፍ የሚፈስ ካፒታል” አይነት አባባሎች ሰፋ ያለ ማብራርያ የሚጠይቁ ናቸው።

ነገር ግን ማስታወስ ያለብን ነገር ቢኖር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጉዳይ የተለየ ተአምር ያለው ነገር አለመሆኑን ነው። የጀርመን ኢኮኖሚያዊ ተአምር ተብሎ ስለሚገለጸው የሁለተኛው አለም ጦርነት ውድመትን ተከትሎ ጀርመን ስላስመዘገበችው ማንሰራራት በተመለከተ በጋዜጦች ብዙ አንብባችኋል። ይህ ግን ተአምረኛ ነገር አይደለም። የነጻ ገበያ ኢኮኖሚያዊ መርሆች አተገባበር ውጤት ነው፣ የካፒታሊዝም መንገድ ውጤት ነው(ምንም እንኳ ካፒታሊዝም ሙሉ በሙሉ እና በሁሉም ረገድ የተተገበረ ባይሆንም)። ሁሉም ሀገር ተመሳሳይ ኢኮኖሚያዊ “ተዓምር” ማሳለፍ የሚችል ሲሆን አስረግጬ ሳልናገር የማላልፈው ነገር ቢኖር ይህ ለውጥ የተአምር ውጤት ሳይሆን ከተስማሚ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች መተግበር የተቀዳ ውጤት መሆኑን ነው።