5ኛው ንግግር፡ የውጭ ኢንቬስትመንት

የውጭ ኢንቬስትመንት

አንዳንዶች የኢኮኖሚ ነጻነት ፕሮግራሞችን አሉታዊ ፕሮግራሞች ይሏቸዋል። እንዲህ ይላሉ፦ “እናነተ ሊብራሎች ምንድነው ከልብ የምትፈልጉት? ሶሻሊዝምን፣ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን፣ የገንዘብ ግሽበትን፣ የሠራተኛ ማኅበር ዓመጽን፣ ከውጭ የሚገባ ምርት ላይ የሚጣል ግብርን ትቃወማላችሁ። ለሁሉም ነገር መልሳቹህ ‘አይሆንም’ ነው።”

ይህ መግለጫ ግን ችግሩን ከአንድ ጎን ብቻ የሚያይና እና ጥልቀት የጎደለው አገላለዝ ነው እላለሁ። ምክንያቱም የሊበራል ፕሮግራምን በአዎንታዊ መንገድ ማቅረብ ይቻላልና። አንድ ሰው “እኔ የሳንሱር ተቃዋሚ ነኝ” ቢል አሉታዊ አይደለም፤ ፍላጎቱ ደራስያን ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት ማተም የሚፈልጉትን የመወሰን መብት እንዲኖራቸው ነው። ይህ አሉታዊነት ሊባል አይችልም፤ ይህ በትክክል ነፃነት ነው። (በእርግጥ እኔ “ሊበራል" የሚለውን ቃል የምጠቀመው ከኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ነው፤ በጥንታዊው የክላሲካል ቃል ፍቺው ነው።)

በዛሬው ግዜ ብዙ ሰዎች በብዙ አገሮች መካከል የሚስተዋለው ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ልዩነት ልክ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በታላቋ ብሪታንያ የነበረው ሁኔታ ዛሬ በሕንድ ከሚታየው ሁኔታ እጅግ የከፋ ነበር። ነገር ግን ብሪታናዊያን በ1750 ራሳቸውን “ያላደግን" ወይም “ኋላቀር" ብለው አልጠሩም፣ ምክንያቱም በኢኮኖሚያዊ ሁኔታቸው ከነሱ የሚሻሉ አገራትን ከራሳቸው የሚያነጻጽሩበት እድል አልነበራቸውም። በአሁኑ ግዜ ሰዎች የኑሮ ደረጃቸው ከዩናይትድ ስቴትስ አማካይ የኑሮ ደረጃ ጋር መቀራረብ ባለመቻሉ የራሳቸው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ችግር ያለበት እንደሆነ ያስባሉ። ከነዚህ አገሮች መካከል ብዙዎቹ ራሳቸውን “ታዳጊ አገር" ብለው የሚጠሩ ሲሆን በዚህ ስያሜ ምክንያት “የበለጸጉ" ወይም “ከመጠን በላይ የበለጸጉ" ተብለው ከሚታወቁ አገሮች እርዳታ ይጠይቃሉ።

የተሻሉ መሣሪያዎች ምርትን ይጨምራሉ

የዚህን ሁኔታ እውነታ ላብራራ። ታዳጊ ተብለው በሚታወቁ አገሮች ውስጥ የሚገኘው የኑሮ ደረጃ ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ለተመሳሳይ ዓይነት ሥራ የሚከፈለው አማካይ ደሞዝ በምዕራብ አውሮፓ፣ በካናዳ፣ በጃፓንና በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ ካለው ያነሰ በመሆኑ ነው። ለዚህ ልዩነት ምክንያቶች ለማግኘት ከሞከርን በሠራተኞቹ ወይም በቅጥረኞች ዝቅተኝነት አለመሆኑን መገንዘብ አለብን። በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ አንዳንድ የሰራተኛ ቡድኖች ከሌሎች ሰዎች እንሻላለን ብሎ የማመን ዝንባሌ አለ - እሱም ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ደመወዝ የሚያገኙት በብቃታቸው ነው የሚል።

በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ አንዳንድ የሰራተኛ ቡድኖች ከሌሎች ሰዎች እንሻላለን ብሎ የማመን ዝንባሌ አለ - እሱም ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ደመወዝ የሚያገኙት በብቃታቸው ነው የሚል።

አንድ አሜሪካዊ ሠራተኛ ከፍተኛ ደመወዝ እንዲያገኝ ያስቻለው የግል ባህሪው ሳይሆን የሀገሪቱ ሁኔታ መሆኑን እንዲገነዘብ እንደ ጣልያን ያለችን ሀገር ብቻ መጎብኘት በቂው ነው። አንድ የሲሲሊ ሰው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከሄደ ብዙም ሳይቆይ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተለመደውን የደመወዝ መጠን ማግኘት ይችላል። እና ይህ ተመሳሳይ ሰው ወደ ሲሲሊ ከተመለሰ የዩናይትድ ስቴትስ ጉብኝቱ ከሀገሩ ልጆች የተሻለ ደመወዝ የሚያስገኘውን ችሎታ እንዳልሰጠው ይገነዘባል።

እንዲሁም ይህ ሁኔታ ከዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ያሉ ሥራ ፈጣሪዎችን የበታች አድርጎ በማሰብ ሊብራራ አይችልም። ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከካናዳ፣ ከምዕራብ አውሮፓና ከአንዳንድ የእስያ ክፍሎች ውጪ ያሉት አብዛኞቹ ሀገራት ያሏቸው ፋብሪካዎች እና መሳሪያዎች እንዲሁም የሚጠቀሙባቸው የቴክኖሎጂ ዘዴዎች ከዩናይትድ ስቴትስ በንፅፅር ያነሡ መሆናቸው አይካድም። ነገር ግን ይህ የሆነበት ምክንያት የነዚህ "ያልበለፅጉ" አገሮች ሥራ ፈጣሪዎች ባላቸው የእውቀት ማነስ አይደለም። በአሜሪካ እና በካናዳ ያሉ ፋብሪካዎች በጣም የተሻሉ መሆናቸውን በደንብ ያውቃሉ። እነሱ እራሳቸው ስለ ቴክኖሎጂ ማወቅ ያለባቸውን ሁሉ ያውቃሉ፣ ካላወቁ ደግሞ ይህ እውቀት ከሚሰራጭባቸው መማሪያ መጽሐፍት እና የቴክኒክ መጽሔቶች ማወቅ ያለባቸውን ለመማር ዕድሉ አላቸው።

አሁንም ልዩነቱ የግለሰብ የበታችነት ወይም ድንቁርና አይደለም። ልዩነቱ የካፒታል አቅርቦት እና የካፒታል እቃዎች ብዛት ነው። በሌላ አነጋገር በነዋሪው ልክ የሚፈሰው የካፒታል መጠን ከታዳጊ አገሮች ይልቅ በበለጸጉት አገራት የበለጠ ነው።

​​አንድ ነጋዴ ለአንድ ሠራተኛ የሚከፍለው ደመወዝ ሠራተኛው በምርቱ ዋጋ ላይ ከሚጨምረው በላይ ሊሆን አይችልም። ደንበኞች ለሠራተኛው ተጨማሪ ሥራ መክፈል ፈቃደኛ ከሚሆኑት በላይ አሰሪው ሊከፍለው አይችልም። የበለጠ ከከፈለው ወጪውን ከደንበኞቹ መመለስ አይችልም። እሱ ኪሳራ ያስከትላል እናም ደጋግሜ እንደገለጽኩት እና ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው ኪሳራ ማስተናገድ የጀመረ ነጋዴ የሥራ ስልቱን መለወጥ አለበት ካልሆነ ሙሉ በሙሉ ይከስራል።

ኢኮኖሚስቶች ይህንን ሁኔታ የሚገልጹት" ደመወዝ የሚወሰነው በሰራተኛ ማርጂናል(marginal) ምርታማነት ነው" በማለት ነው። ይህ ቀደም ሲል ለተናገርኩት ሌላ አገላለጽ ነው። የደመወዝ ደረጃ የሚወሰነው የአንድ ሰው ሥራ የምርቱን ዋጋ በሚጨምርበት መጠን ነው። ስራውን በተሻለና ውጤታማነቱን በሚያፈጥን መሣሪያዎች የሚሠራ ሰው በአንድ ሰዓት ውስጥ ማከናወን የሚችለው መጠን፣ ስራውን ዝቅተኛ በሆኑ መሣሪያዎች የሚሰራ ሰው በትመሳሳይ ሰዓት ማከናወን ከሚችለው እጅግ የበለጠ ነው። ዘመናዊ የሆኑ መሳሪያዎች እና ማሽኖች በተገጠሙባቸው የአሜሪካ የጫማ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ አንድ መቶ ሰዎች በሕንድ ውስጥ ባልተራቀቁና ጊዜ ባለፈባቸው መሳሪያዎች ከሚሰሩ አንድ መቶ ሰዎች አንጻር በተመሳሳይ ግዜ የበለጠ ምርት ማምረት መቻላቸው ግልጽ ነው።

በእነዚህ ሁሉ ታዳጊ አገሮች ውስጥ ያሉ አሰሪዎች የተሻሉ መሣሪያዎች የራሳቸውን ኢንተርፕራይዞች የበለጠ ትርፋማ እንደሚያደርጉ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ብዙ እና የተሻሉ ፋብሪካዎችን መገንባት ይፈልጋሉ። ይህን ከማድረግ የሚያግዳቸው ብቸኛው ነገር የካፒታል እጥረት ነው። በታዳጊ እና በበለጸጉት ሀገሮች መካከል ያለው ልዩነት ገጽታው ጊዜያዊ ነው፦ ብሪታንያውያን መቆጠብ የጀመሩት ከሌሎች ሀገሮች ሁሉ አስቀድመው ነው - ካፒታል ማከማቸት እና በንግድ ኢንቬስት ማድረግ የጀመሩትም ቀደም ብለው ነው። ቀደም ብለው በመጀመራቸው ከቀሪው የአውሮፓ አገራት በንፅፅር ከፍ ያለ የኑሮ ደረጃ ነበራቸው። ቀስ በቀስ ሌሎቹ ሃገራት በሙሉ የብሪታንያን ሁኔታ ማጥናት ሲጀምሩ ለታላቋ ብሪታንያ ሀብት መንስኤ የሆነውን ነገር መረዳት አስቸጋሪ አልሆነባቸውም። በዚህም ምክንያት የብሪታንያን የንግድ ዘዴዎች መኮረጅ ጀመሩ።

ሌሎቹ ሃገራት ቆይተው ስለጀመሩ እና ብሪታናውያን ካፒታል ኢንቨስት ማድረጉን ባለማቋረጣቸው በእንግሊዝ እና በእነዚህ ሀገሮች መካከል ትልቅ ልዩነት ኖሮ ቀጥሏል። ነገር ግን የታላቋ ብሪታንያ መሪነት እንዲጠፋ ምክንያት የሆነ አንድ ነገር ተከሰተ።

የብሪታንያ የውጭ ኢንቬስትመንቶች

ክስተቱ የአስራዘጠነኛው ክፍለዘመን ታላቁ ክስተት ሲሆን በአንድ ሀገር ተነጥሎ የተፈጠረ ብቻ አልነበረም። ይህ ታላቅ ክስተት በአስራዘጠነኛው ክፍለዘመን ይተጀመረው የውጭ ኢንቨስትመንት እድገት ነው። እ.ኤ.አ በ1817 ታላቁ እንግሊዛዊ የምጣኔ ሀብት ምሁር ሪካርዶ ካፒታል ማፍሰስ የሚቻለው በእራስ ሀገር መዋዕለ ንዋይ ውስጥ ብቻ እንደሆነ ያምን ነበር። ካፒታሊስቶች በውጭ አገር ኢንቨስት ለማድረግ እንደማይሞክሩ እርግጠኛ ነበር። ከጥቂት አስርተ ዓመታት በኋላ ግን በውጭ አገር የሚደረግ የካፒታል ኢንቨስትመንት በዓለም ጒዳዮች ውስጥ በጣም አስፈላጊ ሚና መጫወት ጀመረ።

ያለ ካፒታል ኢንቬስትመንት በእድገት ከታላቋ ብሪታንያ ያነሱ ሃገራት ብሪታናዊያን በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ እና አጋማሽ ላይ ከጀመሩበት ቴክኖሎጂ ጀምረው፣ ቀስ በቀስ እና ደረጃ በደረጃ (ሁሌም ከነሱ ወደኋላ በቀረ አካሄድ) ብሪታናዊያን የሄዱበትን መንገድ መድገም ይኖርባቸው ነበር።

እነዚህ ሃገራት ታላቋ ብሪታንያ ከመቶ ዓመት በፊት (ከዛም በላይ ሊሆን ይችላል) የደረሰችበትን የቴክኖሎጂ እድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ፣ ብዙ አስርት ዓመታት ይፈጅባቸው ነበር። ግን እነዚህን ሁሉ ሃገራት የረዳቸው ታላቅ ክስተት የውጭ ኢንቬስትመንት ነበር።

የውጭ ኢንቬስመንት የብሪታንያ ካፒታሊስቶች የብሪታንያን ካፒታል በሌሎች የዓለም ክፍሎች እንዲያፈሱ ምክንያት ሆነ። መጀመርያ ኢንቬስት ያደረጉት ከታላቋ ብሪታንያ አንፃር የካፒታል እጥረት ባለባቸው እና በልማታቸው ኋላ ቀር በሆኑ የአውሮፓ አገራት ውስጥ ነበር። የአብዛኞቹ የአውሮፓ ሃገራት እና የዩናይትድ ስቴትስ የባቡር ሃዲዶች የተገነቡት በብሪታን ካፒታል እርዳታ መሆኑ በደንብ የሚታወቅ እውነታ ነው። በዚህች ሀገር በአርጀንቲናም ተመሳሳይ ነገር እንደተከሰተ ታውቃላችሁ።

በሁሉም የአውሮፓ ከተሞች ያሉ የጋዝ ኩባንያዎች የብሪታናውያን ነበሩ። በ1870ዎቹ አጋማሽ አንድ እንግሊዛዊ ደራሲና ገጣሚ የሀገሩን ሰዎች ተቸ። እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ብሪታናውያን የቀድሞ ኃይላቸውን አጥተዋል፤ አዳዲስ ሐሳቦችም የላቸውም። ከአሁን በኋላ በዓለም ላይ ታላቅ ወይም ግንባር ቀደም ሕዝብ አይደሉም።” ለዚህ ታላቁ ሶሺዮሎጂስት ሄርበርት ስፔንሰር እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “የአውሮፓን አህጉር ተመልከቱ። ሁሉም የአውሮፓ ወና ከተሞች ብርሃን ያላቸው የብሪታንያ የጋዝ ኩባንያ ጋዝ ስለሚያቀርብላቸው ነው።” ይህ የሆነው ለኛ አሁን “ጥንት” በሚመስለን የጋዝ መብራት ዘመን ነው። ሄርበርት ስፔንሰር ለዚህ ብሪታናዊ ተቺ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ሲል ያክላል፦ “ጀርመኖች ብሪታናውያንን በርቀት ቀድመዋል ትላለህ። ግን ጀርመንን ተመልከት፤ የጀርመን ግዛት ዋና ከተማ በርሊን እንኳ የብሪታን የጋዝ ኩባንያ ወሯት ጎዳናዋን ባያበራ ይሄኔ ጨለማ ውስጥ ነበረች።”

በተመሳሳይ መልኩ የብሪታንያ ካፒታል በዩናይትድ ስቴትስ የባቡር ሀዲዶችንና በርካታ የኢንዱስትሪ ዘርፎችን አዳብሯል። እናም በእርግጠኝነት አንድ አገር ወደ ውስጥ ካፒታል እስካስገባ ድረስ የኢኮኖሚ ባለሙያ ያልሆኑ ሰዎች የንግድ ሚዛኑን “አጥጋቢ ያልሆነ” ይሉታል። ይህ ማለት ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ከኤክስፖርት በላይ ናቸው ማለት ነው።