መቅድም
— ፍሪትዝ ማህሉፕ ፕሪንስተን እ.አ.አ 1979ይህ መጽሀፍ ጸሃፊው በደጋፊዎቹ የሚደነቅበትን እና በተቀናቃኞቹ የሚጠላበትን፣ የጸሃፊውን መሰረታዊ ሀሳቦች በተሟላ መልኩ ያቀርባል። ምንም እንኳ እነዚህ 6 ንግግሮች እራሳቸውን የቻሉ ድርሰቶች ሊወጣቸው ቢችልም በተቀናጀ መልክ ተከታትለው መቅረባቸው ለአንባቢው በጥሩ ሁኔታ ተዋቅሮ የተገነባ ህንጻን የመመልከት ያህል ያስደስታል።
እ.አ.አ በረፋዱ 1958 ባለቤቴ በዶክተር አልቤርቶ ቤንጋስሊንች ጋባዥነት አርጀንቲና መቶ ንግግሮችን እንዲያቀርብ ሲጋበዝ፣ አብሬው እንድሄድ ተጠይቄ ነበር። ይህ መጽሃፍ ባለቤቴ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የአርጀንቲና ተማሪዎች የሰጠውን ንግግር በጽሁፍ መልክ ያቀርባል።
አርጀንቲና የደረስነው ፔሮን ሀገሩን ተገዶ ከመልቀቁ ከተወሰኑ አመታት በኋላ ነበር። አውዳሚው አገዛዙ የአርጀንቲናን የኢኮኖሚ ከስር መሰረቱ ያጠፋ ነበር። ሀገሪቱ ለአዲስ ሀሳቦች ክፍት ነበረች፤ ባለቤቴም ይህን ለማሟላት እኩል ዝግጁ ነበር።
ንግግሩን ያረገው በግዙፉ የቦነስ አይረስ ዩኒቨርስቲ ንግግር አዳራሽ ሲሆን ንግግሩን ያካሄደው በእንግሊዘኛ ነበር። በሚናገርበት ግዜ በሁለት ተጓዳኝ ክፍሎች ቃላቱ ወደ ስፓኒሽ እየተተረጎሙ በጆሮ ማዳመጫ ለሚሰሙ ተማሪዎች ይተላለፍ ነበር። ሉድዊግ ቮን ሚዝስ ስለ ካፒታሊዝም፣ ሶሻሊዝም፣ መንግስት ጣልቃ ገብነት፣ ኮሙኒዝም፣ ፋሺዝም፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና ስለ አምባገነንነት አደጋዎች ያለ ምንም ገደብ ተናገረ። እነዚህ ባለቤቴን ያዳምጡ የነበሩ ወጣት አድማጮች ስለገበያ ነጻነትም ይሁን ስለ ግለሰብ ነጻነት እዚህ ግባ የሚባል እውቀት አልነበራቸውም። ከሉድዊግ ቮን ሚዝስ ጋር ያሳለፍኩት አመታት በሚባለው መጽሃፌ ስለ ሁኔታው እንደተናገርኩት፣ “በግዜው ኮሙኒዝም እና ፋሺዝምን ባለቤቴ አጥቅቶ እንደተናገረው ሌላ ሰው ላጥቃው ቢል ፖሊሶች መተው እስር ቤት ይወስዱት ነበር፤ ስብስቡም በሀይል ይበተን ነበር።”
የታዳሚው ስሜት መስኮት ተከፍቶ ንጹህ አየር ይግባ የተባለ ያህል ነበር። ንግግሩን ያካሄደው ምንም ማስታወሻ ጽሁፍ ሳይዝ ነበር። እንደ ሁሌም ሃሳቡ ብጣሽ ወረቀት ላይ በተጻፉ በተወሰኑ ቃላት ነበር የሚመራው። መናገር የሚፈልገውን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። በንጽጽሩ ቀለል ያሉ ቃላትን በመጠቀም ስለስራው ለማያውቁ ሰዎች ሀሳቡን በስኬት ማስተላለፍ ችሎ ነበር።
ንግግሮቹ በቴፕ ተቀርጸው ነበር። የድምጽ ቅጂዎቹ ቆይተው ስፓኒሽ በምትናገር ጸሃፊ የተተረጎሙ ሲሆን፣ ጽሁፉን ያገኘሁት ባለቤቴ ከሞተ በኋላ ካገኘኋቸው ወረቀቶች መሃል ነው። የጽሁፍ ግልባጩን ማንበብ እነዛ አርጀንቲናውያን የባለቤቴን ቃላት የተቀበሉበትን ልዩ ስሜት ቁልጭ አድርጌ እንዳስታውስ ረዳኝ። ኢኮኖሚስት እንዳልሆነ ሰው፣ እኔ እንደሚመስለኝ፣ በደቡብ አሜሪካ ለተራው ህዝብ ያስተላለፋቸው እነዚህ ንግግሮች ከሌሎቹ ንድፈ ሃሳባዊ ጽሁፎቹ አንጻር ለመረዳት ቀላል ናቸው። በጣም ጠቃሚ ይዘት እንደነበራቸው እና ለዛሬ እና ለነገ አስፈላጊ የሆኑ ሃሳቦች የያዙ መስሎ ስለተሰማኝ ለሰፊው ህዝብ እንዲቀርቡ አሰብኩ።
ባለቤቴ እነዚህን የንግግር ግልባጮች በመጽሃፍ እትም መልክ እንዲቀርቡ አድርጎ ባለማዘጋጀቱ የዚህ ስራ ለኔ ወድቋል። እያንዳንዱ አረፍተ ነገር ትርጉሙን የጠበቀ እንዲሆን፣ ይዘቱ ምንም እንዳይለወጥ እና ለአንባቢዎቹ የሚታወቀውን የባለቤቴን አነጋገር ዘይቤ ላለመቀየር ጠንቅቄ ሰርቻለሁ። እኔ የጨመርኩት አስተዋጽኦ ቢኖር አረፍተ ነገሮችን ማገናኘት እና መደበኛ ባልሆነ ንግግር የሚጠቀሱ አንዳንድ ቃላትን መቀነስ ነው። እነዚህን ንግግሮች ወደ መጽሃፍ የመቀየር ጥረቴ ስኬታማ ከተባለ ሊባል ያስቻለው በያንዳንዱ አረፍተ ነገር የባለቤቴን ድምጽ፣ እሱ ሲናገር ስለምሰማው ነው። እሱ ለኔ ህያው ነው፣ ገደቡን የተላለፈ መንግስት ስለሚጋርጠው ክፋት እና አደጋ በሚሰጠው ግልጽ ማብራርያ ውስጥ እሱ ህያው ነው፣ በአምባገነንነት እና በመንግስት ጣልቃ ገብነት መሃከል ስላለው ልዩነት በሚያስረዳበት ስፋት እና ግልጽነት ውስጥ እሱ ህያው ነው፣ ተጠቃሽ የታሪክ ሰዎችን በሚያነሳበት ወግ ውስጥ እሱ ህያው ነው፣ ያለፉ ግዜያትን ወደ ህይወት ያሚያመጣባቸው የሱ ቁጥብ ቃላት ውስጥ እሱ ህያው ነው።
በዚህ ተግባር ላገዘኝ ጥሩ ጓደኛዬን ጆርጅ ኮተርን ላመሰግን እወዳለሁ። ጽሁፎችን ለእትም የማዘጋጀት ልምዱ እና ስለ ባለቤቴ ንድፈ ሃሳቦች ያለው እውቀት ይህን መጽሃፍ ለማዘጋጀት እጅግ ረድተውኛል።
ተስፋዬ እነዚህ ንግግሮች በምሁራን ብቻ ሳይሆን የባለቤቴ አድናቂ በሆነው ሰፊው ማህበረሰብ ዘንድ ተነባቢነት እንዲያገኙ ነው። ከዛም አልፎ በአለም ዙርያ ለሚገኙ ወጣት አንባቢዎች፣ በተለይ ለሁለተኛ እና ከፍተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለንባብነት ይቀርባል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ማርግሪት ቮን ሚዝስ ኒው ዮርክ እ.ኤ.አ ጁን 2006