ኢንፍሌሽን
የካቪያር አቅርቦት የድንች ያህል በርካታ ቢሆን የካቪያር የገበያ ዋጋ - ማለትም ካቪያር በገንዘብ ወይም ከሌሎች ምርቶች ጋር የሚለዋወጥበት ልዩነት - ይቀየር ነበር። ያን ግዜ ካቪያርን ለማግኘት የሚከፈለው መስእዋትነት ካሁኑ ይቀንስ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ በኢኮኖሚ የሚዘዋወረው የገንዘብ መጠን(quantity of money) ሲጨምር የገንዘቡ መግዣ አቅም አብሮ ይወርዳል፣ በአንድ የገንዘብ አሃዝ የሚገዛው የምርት መጠን አብሮ ይቀንሳል።
የወርቅ እና ብር ማዕድን በስፋት የተስፋፋባት የ16ኛዋ ክፍለዘመን አሜሪካ እነዚህን ውድ ብረቶች በከፍተኛ ደረጃ ወደ አውሮፓ ትልክ ነበር። በዚህም ምክንያት በአውሮፓ የተከሰተው የውድ ብረት መጠን መጨመር በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ አስከስቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ መንግስት በአሁኑ ዘመን በማህበረሰቡ የሚዘዋወረውን የወረቀት ገንዘብ መጠን ሲጨምር የገንዘቡ መግዣ አቅም አብሮ መቀነስ ይጀምራል። የምርቶች ዋጋም አብሮ ይጨምራል። ኢንፍሌሽን የሚባለው ይህ ነው።
አለመታደል ሆኖ ግን በአሜሪካም ሆነ በሌሎች ሃገራት ለኢንፍሌሽን መንስኤ ተደርጎ የሚታሰበው የገንዘብ መጠን ጭማሪ ከመሆን ይልቅ የምርት ዋጋ መወደድ ነው።
ነገር ግን በገንዘብ መጠን እና በኑሮ ውድነት እንዲሁም በገንዘብ እና በምርት፣ ሸቀጥ እና አገልግሎት ያለውን ዝምድና ውድቅ ሊያደርግ የሚችል ጠለቅ ያለ ሃሳብ ቀርቦ አያውቅም። በዛሬ ዘመን ቴክኖሎጂ ቁጥር የተለጠፈበት የገንዘብ ወረቀትን እንዲሁ ከማተም የሚቀል ነገር የለም። በአሜሪካ ሁሉም የገንዘብ ወረቀቶች ተመሳሳይ ልኬት ያላቸው በመሆኑ የአንድ ሺህ ብር ወረቀት ማተም አንድ ብር ከማተም የተለየ ወጪ የለውም። ሁለቱንም የብር መጠኖች ለማተም ተመሳሳይ የወረቀት እና የቀለም መጠን መኖሩ በቂ ነው።
የማተምያ ቤት ገንዘብ
ለመጀመርያ ግዜ የባንክ ወረቀቶችን የመገበያያ ገንዘብ ለማድረግ የተሞከረው በአስራስምንተኛው ክፍለዘመን ነበር። የዚህ ሙከራ መንስኤ ባንክ አስተዳዳሪዎች ሃብትን ከምንም መፍጠር የሚያስችላችል ሚስጥራዊ ችሎታ እንዳላቸው የበርካታ ሃገሮች መንግስታት ማመናቸው ነው። በግዜው የመገበያያ ገንዘብ የወርቅ እና የብር ሳንቲሞች የነበሩ ሲሆን የባንክ ወረቀቶችን በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ገንዘብ መቀየር ይቻላል ተብሎ ይታሰብ ነበር። በዚህም ምክንያት በገንዘብ ችግር ይንገላቱ የነበሩት የአስራስምንተኛው ክፍለዘመን መንግስታት የችግሩ መፍትሄ ብልህ የባንክ አስተዳዳሪ የማግኘት ጉዳይ አድርገው ያስቡ ነበር።
የፈረንሳይ አብዮት ከመፈንዳቱ ከተወሰኑ አመታት በፊት የፈረንሳይ ንጉስ የሀገሪቱ መኳንንት ከተጠመዱበት የገንዘብ ችግር ያወጣቸው ዘንድ ብልህ ነው ብሎ ያሰበውን የባንክ አስተዳዳሪ ከፍተኛ ሹምት ይሰጠዋል። ይህ ሰውዬ እስከዛ ግዜ ድረስ ፈረንሳይን ካስተዳደሩ ሰዎች በሁሉም ገጽታ ተቃራኒ ነበር። አንደኛ ጃኩዌስ ኔከር ፈረንሳዊ አይደለም። ጄኔቭ የተወለደ ስዊዘርላንዳዊ ነው። ሁለተኛ፣ ዘር ግንዱ የተመዘዘው ከመኳንንት ሳይሆን ከተራው ህዝብ ነው። ግን ከሁሉም ልዩነቶቹ በአስራስምንተኛው ክፍለዘመን ፈረንሳይ ገዝፎ እንዲለይ ያደረገው፣ በእምነቱ ካቶሊክ ሳይሆን ፕሮቴስታንት መሆኑ ነው። በዚህ ሁኔታ ነበር የታዋቂዋ ማዳም ዲ ስታኤል አባት፣ ጌታ ኔከር የፈረንሳይ ገንዘብ ሚንስተር ሆኖ የተሾመው። የሀገሪቱን የገንዘብ(finance) ችግር ይፈታል ተብሎ ከፍተኛ እምነት ተጥሎበት ነበር። ግን ምንም እንኳ ጌታ ኔከር በሀገሪቱ ከፍተኛ ድጋፍ ቢኖረውም የሀገሩን ጥሬ ገንዘብ ከባዶነት ሊታደገው አልቻለም። የኔከር ትልቁ ስህተት ግብር ሳይጨምር የአሜሪካ ሰፋሪዎች እንግሊዝ ላይ ባወጁት የነጻነት ጦርነት አሜሪካኖቹን በገንዘብ ለመርዳት መሞከሩ ነበር። ይህ እርምጃ ፈረንሳይ ከገባችበት የገንዘብ ችግር ለመውጣት በምታደርገው ጥረት እንቅፋት ሆኖ አልፏል።
የገንዘብ ችግር ያጋጠመው መንግስት ችግሩን የሚፈታበት ሚስጥረኛ መንገድ የለዉም። ገንዘብ ሲያስፈልገው የሀገሩ ዜጎች ላይ ግብር በመጨመር ገንዘብ ማግኘት ይችላል። ወይም በአንዳንድ ልዩ ሁኔታ ገንዘቡ ካላቸው ሰዎች ገንዘቡን መበደር ይችላል። ነገር ግን ብዙ መንግስታት(አብዛኛው ማለት እንችላለን) ገንዘብ የምናገኝበት ሌላ መንገድ አለ ብለው ያስባሉ። ይህም መንገድ ገንዝብ ማተም ነው።
መንግስት(ሆስፒታል እንደመገንባት አይነት) ጠቃሚ ነገር ለመስራት ሲያስብ ተጨማሪ ግብር ዜጎች ላይ በመጣል ከሚሰበስበው ተጨማሪ ገቢ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለፕሮጀክቱ ማዋል ይችላል። ይህ ሲሆን ሃገሪቱ ላይ የተለየ የዋጋ ንረት አይፈጠርም። የዚህም ምክንያት ለሌላ ወጪ ሊውል የነበረ ገንዘብ ለሆስፒታል ግንባታ በመዋሉ እና በዛም ምክንያት ዜጎች ወጪያቸውን ለመቀነስ በመገደዳቸው ነው። ግብር ከፋዩ ለፍጆታ፣ ለመዋዕለ ንዋይ ወይም ለቁጠባ የሚያውለውን ገንዘብ ለመቀነስ ይገደዳል። ገበያ ላይ ግለሰብ በመንግስት ይተካል(ግለሰቦች የሚገዙትን ይቀንሳሉ መንግስት የሚገዛውን ይጨምራል)። መንግስት እና ግለሰብ የሚገዟችው ነገሮች መለያየታቸው ባያጠያይቅም መንግስት ሆስፒታል በመስራቱ በአማካይ ተጠቃሽ የሚባል የዋጋ ንረት አይፈጥርም።
ሆስፒታል መገንባትን እንደምሳሌ የጠቀስኩት “መንግስት ገንዘቡን ለጥሩ ወይም ለመጥፎ ነገር ማዋሉ ልዩነት ይፈጥራል” በማለት የሚከራከሩ ሰዎች በመኖራቸው ነው። መንግስት የሚያትመውን ገንዘብ ሁሌም ለጥሩ ነገር(ሁሉ ሰው ለሚስማማበት ነገር) ያውላል ብለን ለግዜው እንነሳ። የምንደርስበት ድምዳሜ አይለወጥም። ምክንያቱም የዋጋ ንረት(ኢንፍሌሽን) ብለን ለምንጠራው ነገር መንስኤ የሆነው መንግስት አዲሱን ገንዘብ የሚያገኝበት መንገድ እንጂ ገንዘቡን የሚያውልበት ቦታ አይደለም።
ለምሳሌ መንግስት በግብር የሰበሰበውን ገንዘብ ተጠቅሞ ኢንፍሌሽን ሳይፈጥር አዲስ ሰራተኞችን መቅጠር ወይም ላሉት ሰራተኞች ደሞዝ ጭማሪ ማድረግ ይችላል። እነዚህ ደሞዝ የተጨመረላቸው ሰራተኞች የመግዛት አቅማቸው አብሮ ይጨምራል። መንግስት ዜጎች ላይ ግብር በመጨመር የሚሰበስበውን ተጨማሪ ገቢ ለመንግስት ቅጥረኞች ደሞዝ ጭማሪ ሲያውለው የግብር ከፋዮች የመግዛት አቅም ይወርዳል፤ የመንግስት ሰራተኞች የመግዛት አቅም ይጨምራል። የገበያ ዋጋ ወይም የኑሮ ውድነት ግን አይቀየርም።
ነገር ግን ለደሞዝ ጭማሪ የዋለው ገንዘብ በግብር የተሰበሰበ ሳይሆን አዲስ የታተመ ገንዘብ ሲሆን በቀሪው ማህበረሰብ እጅ ያለው ገንዘብ ሳይቀንስ የተወሰኑ ሰዎች እጅ ተጨማሪ ገንዘብ ተለይቶ ይገባል። አዲስ የገንዘብ እትም እጃቸው የገባ ሰዎች ከሌሎች ሸማቾች እኩል በግዢ መወዳደር ይጀምራሉ። በዚህ ተጨማሪ ገንዘብ እንጂ ተጨማሪ ምርት በሌለበት ሁኔታ እናም አዲስ ገንዘብ ተጠቅመው ተጨማሪ ምርት መግዛት የሚችሉ ሰዎች በተፈጠሩበት ሁኔታ በገበያው ያለው የምርት ፍላጎት አብሮ ይጨምራል። በዚህ ሁኔታ የምርቶችም ዋጋ ተያይዞ ይወጣል። አዲሱ ገንዘብ የትኛውም አይነት ምርት ላይ ቢውል እንኳ የገበያ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ማምለጫ የሌለው ውጤት ነው።
ደረጃ በደረጃ የሚከሰት የዋጋ ጭማሪ
ይበልጥ ደግሞ ይህ የዋጋ ጭማሪ ደረጃ በደረጃ የሚፈጠር እንጂ “የዋጋዎች መጠን”(price level) ጭማሪ ተብሎ የሚገለጸው አይነት ጭማሪ አይደለም። “የዋጋዎች መጠን” የሚለውን ዘይቤአዊ አነጋገር በፍጹም መጠቀም አይገባም።
የዋጋዎች መጠን ብለው ሰዎች ሲያወሩ ዋጋን ብርጭቆ ውስጥ እንዳለ ውሃ፣ መጠኑ ከውሃው እኩል አብሮ ከፍ እና ዝቅ የሚል አድርገው በማሰብ ነው፡። ዋጋዎች ላይ ግን ጭማሪ ሲታይ በተመሳሳይ ደረጃም ሆነ በተመሳሳይ ፍጥነት አይደለም። ሁሌም በተለየ ፍጥነት ዋጋቸው የሚቀየር፣ ከሌላ ምርት አንጻር ዋጋቸው በፍጥነት የሚጨምር እና የሚቀንስ የምርት አይነቶች አሉ። ይህ ሁኔታ ምክንያት አለው።
እንደ ምሳሌ አዲስ የታተመ ገንዘብ ስለሚረከበው የመንግስት ቅጥረኛ እናስብ። የሰው ልጅ ገበያ ሲወጣ ዛሬ የገዛቸውን ምርቶች በተመሳሳይ ብዛት እና አይነት ነገ አይገዛም። አዲስ ታትሞ የሚሰራጨው ገንዘብ ሁሉንም ምርት እና አገልግሎት እኩል አያሳድድም። የተወሰኑ ምርቶችን ለይቶ ለመግዛት ይውላል። በዚህ ምክንያት የነዚህ ምርቶች ዋጋ የሚጨምር ሲሆን የሌሎች ምርቶች ዋጋ ደግሞ በአንጻሩ አዲሱ ገንዘብ ከመታተሙ በፊት በነበረው ዋጋ ይቀጥላል። ስለዚህ ኢንፍሌሽን ሲፈጠር ጫናው ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ላይ እኩል አይሆንም። አዲሱን ገንዘብ ቀድመው የሚያገኙ ሰዎች ለአጭር ግዜም ቢሆን ልዩ ጥቅም ያገኛሉ።
ጦርነት ያወጀ መንግስት ጦር መሳርያ ለመግዛት ብሎ ገንዘብ ሲያትም የጦር አምራች ኢንዱስትሪ እና ሰራተኞቹ የአዲሱ ገንዝብ የመጀመርያ ተረካቢዎች ይሆናሉ። የዚህ ግዜ እነዚህ ሰዎች ምቹ ቦታ ላይ ናቸው። አዲስ ገንዘብ ተረካቢ በመሆናቸው ከፍ ያለ ትርፍ እና ደሞዝ ይኖራቸዋል። ተጨማሪም ምርት መግዛት ይጀምራሉ።
ለጦር አምራቹ ዘርፍ ምርት እና አገልግሎት የሚሸጠው ሁለተኛው የማህበረሰብ ክፍልም ቢሆን ኢንፍሌሽንን እንደ ጥሩ ነገር ያየዋል። ገበያው ጨምሮለት እንዴት አያየውም? ጦር መሳርያ የሚመረትበት ሰፈር የሚገኝ የምግብ ቤት ባለቤት ቢጠየቅ እንዲህ ሊመልስ ይችላል፦ “አስደናቂ ነው። የኢንዱስትሪው ሰራተኞች ተጨማሪ ገንዘብ አላቸው። አሁን ከበፊቱ በበለጠ የምግብ ቤቴ ተጠቃሚ ናቸው። ደስተኛ ነኝ።” በሁኔታው የሚያዝንበት ምክንያት የለውም።
እውነታው ግን እንደዚህ ነው፤ አዲሱ ገንዘብ ቀድሞ የደረሳቸው ሰዎች ሲሸምቱ የሚሸምቱበት ዋጋ ኢንፍሌሽን ዋጋ ጭማሪ ከምፍጠሩ በፊት በነበረው ዋጋ ነው። በኢንፍሌሽን ዋዜማ በነበረው ዋጋ ተጨማሪ ምርት እና አገልግሎት መግዛት ይችላሉ። ኢንፍሌሽን ግን ደረጃ በደረጃ ከአንዱ የማህበረሰብ ክፍል ወደ ሌላው ስራውን ይቀጥላል። በኢንፍሌሽን ማለዳ አዲስ የታተመ ገንዝብ ያገኙ ሰዎች የምርት ዋጋ ሳይጨምር ተጨማሪ ምርት መግዛት በመቻላቸው ተጠቃሚዎች ናቸው።
በአንጻሩ ደግሞ ይህ አዲስ ገንዝብ ዘግይቶ የሚደርሳቸው የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ተጎጂ ናቸው። አዲሱ ገንዘብ እነሱ ጋር ከመድረሱ በፊት ለተለያዩ(ወይም ለሁሉም) ምርቶች ተጨማሪ ዋጋ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ። ምንም አይነት ወይም ከገበያው የሚመጣጠን የገቢ ጭማሪ ሳያገኙ ለምርት እና አገልግሎቶች ተጨማሪ ዋጋ ከመክፈል ውጭ አማራጭ አይኖራቸውም።
አሜሪካን በሁለተኛው የአለም ጦርነት ግዜ እናንሳ። ኢንፍሌሽን በአንድ በኩል የጦር መሳርያ አምራች ሰራተኞችን፣ የጦር ምርት ኢንዱስትሪን እና የሽጉጥ አምራቾችን የጠቀመ ሲሆን በሌላ በኩል ግን ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ጫና አሳድሮ አልፏል። ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በይበልጥ የኢንፍሌሽን ገፈት ቀማሽ የነበሩት መምህራን እና ካህናት ነበሩ።
ቄሶች በተለምዶ ልከኛ እና ስለ ገንዘብ ማውራት የሌለባቸው፣ አስተማሪዎችም ከደሞዝ ይልቅ ስለሚያስተምሯቸው ልጆች መጨነቅ እንዳለባቸው ስለሚታሰብ ትምህርት ቤቶች እና ቤተ ክርስትያናት ደሞዝ መጨመር እንዳለባቸው የተገነዘቡት ዘግይተው ነው፤ እናም ኢንፍሌሽን እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች በተለየ ሁኔታ ቀጥቶ አልፏል። የቤተክርስትያን እና የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች ቆይተው ደሞዝ የጨመሩ ቢሆንም የቀድሞው ኪሳራ እንደነበር አልፏል።
ለረጅም ግዜ እነዚህ ተጎጂ የማህበረሰብ አባላት ገቢያቸው ሳይጨምር የኑሮ ውድነት በመጨመሩ ግዢያቸውን ከለመዱት መቀነስ፣ የሚጠቀሟቸውን ጠቃሚ እና ወደድ ያሉ ምርቶች መጠን ማሳነስ እንዲሁም የሚገዙትን የልብስ ብዛት መቀነስ ነበረባቸው።
ኢንፍሌሽን ሁሌም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እኩል አይነካም። ለአንዳንድ ሰዎች ኢንፍሌሽን ለክፋት አይሰጥም። እንደውም የመጀመርያ አትራፊ በመሆናቸው ኢንፍሌሽን እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሰዎች ይኖራሉ። በቀጣዩ ዳሰሳ ይህ የኢንፍሌሽን ጫና አለመመጣጠን የፖለቲካውን ምህዳር እንዴት እንደሚቀይረው እናያለን።
ኢንፍሌሽን በሚያስከትለው በነዚህ ለውጦች ስር ተጠቃሚና በቀጥታ የሚያተርፉ ሰዎች አሉ። እዚህ ጋር አትራፊ ስል አትራፊዎቹን ለመውቀስ በማሰብ በመጥፎ ትርጓሜ የተናገርኩት አይደለም። የሚወቀስ አካል ቢኖር የኢንፍሌሽን ፈጣሪ መንግስት ነው። እና ሁሌም ኢንፍሌሽን የሚሰጣቸውን ጥቀም(የኢንፍሌሽን ያልተመጣጠነ ሂደት የሚፈጥርላቸውን ልዩ ትርፍ) ለይተው በመረዳት የኢንፍሌሽን መፈጠርን የሚደግፉ ሰዎች ይኖራሉ።
ግብር መጣል ለመነግስት ተመራጭ ዘዴ አይደለም
ግብር መጨመር በዜጎች የማይወደድ እና አስቸጋሪ በመሆኑ መንግስት ኢንፍሌሽንን እንደተሻለ የገንዘብ መሰብሰብያ አማራጭ አድርጎ ሊቆጥር ይችላል። የበርካታ ታላቅ እና ሀብታም ሀገራት ፓርላማዎች የመንግስትን ወጪ መጨመራቸውን ተከትሎ ህግ አውጪዎቻቸው ወጪውን ስለሚሸፍኑበት አዲስ የግብር መጠን ለወራት ሲከራከሩ ይታያሉ። በተለያዩ የግብር አጣጣል ዘዴዎች ላይ ተወያይተው በመጨረሻ ኢንፍሌሽንን ሲመርጡ ይታያሉ።
ነገር ግን ይህን ሲያረጉ ኢንፍሌሽን የሚለውን ቃል ከመጠቀም ይቆጠባሉ። ሀገሩን ወደ ኢንፍሌሽን እየመራ ያለ መሪ ወደ ኢንፍሌሽን እየሄድን ነው ብሎ አያውጅም። ኢንፍሌሽን የሚተገበርበት መንገድ ቴክኒካዊ ውስብስብነት የተጎናጸፈ በመሆኑ ተራው ዜጋ ኢንፍሌሽን መጀመሩን አያውቅም።
የጀርመን ግዛት በመጀመርያው የአለም ጦርነት ማግስት በታሪክ ከታዩ ከፍተኛ የኢንፍሌሽን ክስተቶች መሃል አንዱ የሆነውን ኢንፍሌሽን አስተናግዳለች። በጦርነቱ ግዜ የተመዘገበው ኢንፍሌሽን ጉዳቱ መለስተኛ የነበረ ሲሆን ጦርነቱን ተከትሎ የተፈጠረው ኢንፍሌሽን ግን አውዳሚ ነበር። ይህ ሲፈጠር መንግስት ወደ ኢንፍሌሽን እየተጓዝን ነው ብሎ አላወጀም። ይልቅ መንግስት ከማዕከላዊ ባንክ በተዘዋዋሪ መንገድ ገንዘብ ተበደረ። ማዕከላዊ ባንኩ ገንዘቡን ከየት አግኝቶ እንደሚያስረክበው መንግስት አልጠየቀም። ማዕከላዊ ባንኩ በቀላሉ ገንዘብ ማተም ጀመረ።
በአሁኑ ዘመን የቼክ ደብተር በመኖሩ ኢንፍሌሽን የሚተገበርበት ቴክኒካዊ መንገድ ይበልጥ ተወሳስቧል። የዛሬው መንገድ የተለየ ቢሆንም ግን ውጤቱ ተመሳሳይ ነው። በአንድ የወረቀት ፊርማ መንግስት fiat ገንዘብ በመፍጠር በኢኮኖሚው የሚዘዋወረውን የገንዘብ እና ክሬዲት መጠን ይጨምራል፤ መንግስት ትዕዛዝ ማስተላለፍ ብቻ ነው የሚጠበቅበት።
ኢንፍሌሽን ዘላቂ አይደለም
ኢንፍሌሽን በአንዳንድ ሰዎች ላይ የሚፈጥረው ኪሳራም ሆነ የሚያስከትለው የዋጋ ንረት መጀመርያ አካባቢ ለመንግስት ግድ አይሰጠውም። ኢንፍሌሽን ለህግ አውጪዎች ድንቀኛ ዘዴ ነው። ግን ይህ ድንቀኛ ዘዴ አንድ መሰረታዊ ድክመት አለው። ዘላቂነት የለውም። ኢንፍሌሽን ለዘላለም መቀጠል ቢችል ኖሮ መንግስታትን ከኢንፍሌሽን እንዲቆጠቡ መምከር አስፈላጊ ባልሆነ። ግን የኢንፍሌሽን የማያጠራጥር እውነታ ቢፈጥንም ቢዘገይም ፍጻሜው የማያጠያይቅ መሆኑ ነው። ሊቀጥል የማይችል ፖሊሲ ነው።
በረጅም ግዜ እይታ ኢንፍሌሽን በሃገሪቱ ገንዘብ መሰባበር ይቋጫል። መጨረሻው ጀርመን እ.አ.አ በ1923ዓም እንዳሳለፈችው የገንዘብ ውድመት ነው። በኦገስት 1 1914 ቀን የአንድ ዶላር የገበያ ዋጋ 4 የጀርመን ማርክ(በግዜው የጀርመን ገንዘብ የነበረው) እና 20 ፌኒግ(በግዜው የጀርመን ሳንቲም የነበረው) ነበር። ከዘጠኝ አመት እና ሶስት ወር በኋላ በኖቬምበር 1923 የአንድ ዶላር ዋጋ 4.2 ትሪልየን የጀርመን ማርክ ደረሰ። በሌላ ቃል የጀርመን ማርክ ሙሉ ዋጋውን አጥቶ ምንም አይነት ዋጋ አልነበረውም።
ከተወሰኑ አመታት በፊት ታዋቂው ጸሃፊ ጆን ሜይናርድ ኬይንስ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “በረጅም ግዜ እይታ ሁላችንም ሙተናል።” ይህ በእርግጥ እውነት ነው፣ ለመናገር አዝናለሁ። ዋናው ጥያቄ ግን የአጭሩ እይታ(አጭሩ ሩጫ) ምን ያህል አጭር ወይም ረጅም ይሆናል የሚል ነው። ማዳም ዲ ፖምፓዱር በአስራስምንተኛው ዘመን የኖረች ታዋቂ ሴት ስትሆን በሚከተለው አባባል ትታወቃለች "Après nous le dèluge"(ከኛ በኋላ ጎርፉ ይመጣል)። ማዳም ዲ ፖምፓዱር በአጭሩ ሩጫ የመጣ ሞት ግድ አይሰጣትም ነበር ግን እሷን በሹመት የተካችው ማዳም ዱ ባሪ አጭሩን ሩጫ በህይወት ቆይታ በረጅሙ ሩጫ በመቀላት ልትገደል ችላለች። ለብዙ ሰው “ረጅሙ ሩጫ” በፍጥነት ወደ “አጭሩ ሩጫ” ይቀየራል፣ ኢንፍሌሽንም በቀጠለ ቁጥር አጭሩ ሩጫ እየቀረበ ይመጣል።
አጭሩ ሩጫ ምን ያህል ግዜ ይቆያል? ማዕከላዊ ባንክ ኢንፍሌሽንን ምን ያህል ግዜ ሊያስቀጥለው ይችላል? ምናልባት ይዋል ይደር እንጂ ከመርፈዱ በፊት መንግስት ገንዘብ ማተም እንደሚያቆም እና የገንዘብ ዋጋ ማሽቆልቆል እንደሚገታ ህዝቡ እስካመነ ድረስ ኢንፍሌሽን ሊቀጥል ይችላል።
ሰዎች ይህን ማመን ሲያቆሙ፣ መንግስት ያለማቋረጥ ገንዘብ ማተሙን የማቆም ሃሳብ እንደሌለው ሲረዱ፣ የነገ የገበያ ዋጋ ከዛሬው ሁሌም የጨመረ እንደሚሆን ይገነዘባሉ። ያን ግዜ ምርቶችን በተገኘው ዋጋ መግዛት ይጀምራሉ። ይህ ደግሞ የገበያ ዋጋ ይበልጥ እንዲተኮስ በማድረግ የሀገሪቱ የገንዘብ ስርአት እንዲፈርስ ያደርጋል።
በግዜው መላው አለም ይመለከተው ስለነበረው የጀርመን ጉዳይ አመለክታለሁ። የግዜውን ክስተቶች በርካታ መጸሃፍቶች አብራርተዋል።(እኔ ጀርመን ባልሆንም እንደ አውትሪያዊ ብዙ ነገሮችን ከውስጥ መመልከት ችዬ ነበር። ኦስትሪያ ውስጥ ነገሮች ከጀርመን እምብዛም አይሻሉም ነበር። ሌሎች የአውሮፓ ሃገራትም ቢሆኑም እንዲሁ።) ለበርካታ አመታት የጀርመን ህዝብ ኢንፍሌሽን የአጭር ግዜ ክስተት እንደሆነ እና በቅርብ በግዜ እንደሚያበቃ ያምን ነበር። እስከ 1923ቱ የበጋ ወቅት ለ9 አመታት ያህል ይህን ሲያምኑ ቆይተዋል። ከዛ ግን በመጨረሻ መጠራጠር ጀመሩ። ኢንፍሌሽን በቀጠለ ቁጥር ገንዘብ በኪሳቸው ከማቆየት ይልቅ የተገኘውን ነገር በተገኘው ዋጋ መግዛት የተሻለ ብልሃት እንዳለው ተረዱ። በተጨማሪም ብድር መስጠት እንደሌለባቸው እና በተቃራኒው ባለ ዕዳ መሆን እንደሚያዋጣ ደረሱበት። እናም ኢንፍሌሽን እራሱን በመመገብ ቀጠለ።
ጀርመን በዚህ ሁኔታ እ.አ.አ እስከ ኖቬምበር 20፣ 1923 ድረስ ቀጠለች። የኢንፍሌሽን ገንዘብ እውነተኛ ገንዘብ ነው ብሎ ያምን የነበረው የጀርመን ህዝብ ነገሮች እንደተቀየሩ ተረዳ። ኢንፍሌሽን ወደ መገባደጃው በደረሰበት በመኸር ወቅት 1923 የጀርመን ፋብሪካዎች ለሰራተኞቻቸው የቀኑን ደሞዝ ጧት ስራ ከመጀመሩ በፊት ነበር የሚከፍሉት። ደሞዙን ለመቀበል ከባለቤቱ ጋር ይሄድ የነበረው የፋብሪካው ሰራተኛ ደሞዙን(በሚልየኖች የሚቆጠር ገንዘብ) ቀጥታ ለባለቤቱ ያስረክባል። ሚስትም በፍጥነት ወደ ሱቅ በመሄድ ያገኘችውን ነገር ትገዛለች። አብዛኛው ሰው የተረዳውን ነገር እሷም ገብቷታል፤ በአንድ ጀምበር ልዩነት የጀርመን ገንዘብ(ማርክ) የመግዛት አቅሙን 50 በመቶ ያህል ያጣል። ገንዘብ ትኩስ ምድጃ ውስጥ እንደገባ ቸኮሌት በሰው ኪስ እየቀለጠ ነበር። ይህ ኢንፍሌሽን የደረሰበት የመጨረሻው ደረጃ ረጅም ግዜ አልቆየም፤ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ቅዠቱ አበቃ፤ ማርክ ሙሉ በሙሉ ዋጋ ቢስ ሆነ፣ አዲስ ገንዘብ መመስረት ነበረበት።
በወርቅ የተደገፈ የገንዘብ ስርአት
በረጅም ሩጫ ሁላችንም ሞተናል ያለው ጌታ ኬይንስ በሃያኛው ክፍለዘመን ኢንፍሌሽንን ከሚደግፉ በርካታ ጸሃፊዎች አንዱ ነበር። እነዚህ ምሁራን ሁሉም በወርቅ ስለሚደገፈው የገንዘብ ስርአት(ወርቅ ደረጃ/Gold Standard) ተቃውመው ይጽፉ ነበር። ጌታ ኬይንስ በወርቅ የተደገፈውን የገንዘብ ስርአት “አረመኔያዊ ቅርስ”(barbaric relic) በማለት አጥቅቶ ጽፏል። በዛሬውም ግዜ አብዛኛው ሰው በወርቅ ወደሚደገፍ የገንዘብ ስርአት መመለስን እንደ አስቂኝ ሀሳብ ያየዋል። እንደ ምሳሌ ዛሬ አሜሪካ ውስጥ “ቢፈጥንም ቢዘገይም በወርቅ ወደተደገፈ ገንዘብ መመለሳችን አይቀርም” ብትል እንደ ህልመኛ ነው የምትታየው።
ሆኖም ግን በወርቅ የተደገፈ ገንዘብ አንድ ግዙፍ በጎ ገጽታ አለው፤ በወርቅ በተደገፈ የገንዘብ ስርአት ስር የገንዘብ መጠን፣ መንግስት እና ፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚያወጡት ፖሊሲ ነጻ ነው። የሱ ጥቅም ይህ ነው። ገንዘብ አባካኝ ከሆኑ መንግስታት መከላከያ መንገድ ነው። በወርቅ በተደገፈ የገንዘብ ስርአት ስር መንግስት ለአዲስ ነገር ገንዘብ እንዲያወጣ ሲጠየቅ የፋይናንስ ሚንስቴሩ “ገንዘቡን ከየት ነው የማመጣው? መጀመርያ ለዚህ ተጨማሪ ወጪ ገንዘብ ከየት እንደሚመጣ ንገረኝ” ሲል መልስ መስጠት ይችላል።
በኢንፍሌሽናዊ ስርአት ስር ፖለቲከኞች የሚፈልጉትን ገንዘብ እስኪያገኙ ድረስ መንግስትን ገንዘብ እንዲያትም ከማዘዝ የሚቀላቸው ነገር የለም። በወርቅ ደረጃ(Gold standard) ስርአት ስር በአንጻሩ አስተማማኝ መንግስት የመፈጠር የተሻለ እድል አለው። የሃገር መሪ ለህዝቡ እና ለፖለቲከኞች ግብር ሳንጨምር ወጪ መጨመር አንችልም ማለት ይችላል።
በኢንፍሌሽን ስርአት ስር ሰዎች መንግስትን ገደብ የለሽ አቅም እንዳለው ተቋም ይስሉታል፤ መንግስት ማንኛውንም ነገር ማድረግ ይችላል። ህዝብ አዲስ የአውራ ጎዳና መንገድ ቢፈልግ መንግስት እንዲሰራው ይጠበቃል። ግን መንግስት ገንዘቡን ከየት ያገኛል?
በዛሬ አሜሪካ(ከዚህ በፊትም ቢሆን በምክኢንሊ ስር) የወርቅ ደረጃን እና አስተማማኝ ገንዘብን የሚደግፈው ሪፐብሊካን ፓርቲ ሲሆን ዴሞክራት ፓርቲ በአንጻሩ ኢንፍሌሽንን(የወረቀት ገንዘብ ኢንፍሌሽን ሳይሆን የብር ማዕድን ገንዘብ ኢንፍሌሽን) የሚደግፍ ፓርቲ ሆኖ እናገኘዋለን።
ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በ1880ዎቹ አደጋ የደረሰበትን የማህበረሰብ ክፍል 10,000 ዶላር ለመርዳት የቀረበውን ሀሳብ የተቃወሙት የዴሞክራት ፓርቲ አባል የነበሩት የሃገሩ ፕሬዚዳንት ክሊቭላንድ ነበሩ። ተቃውሟቸውን በጽሁፍ መልክ እንደሚከተለው አብራርተዋል፦”መንግስትን መደገፍ የዜጎች ግዴታ ቢሆንም መንግስት ዜጎችን የመደገፍ ግዴታ የለበትም።” ሁሉም የሀገር መሪ ይህን አባባል መስርያ ቤቱ ግድግዳ ላይ ለጥፎ ገንዘብ ሊጠይቁ ለሚመጡ ሰዎች ቢያሳይ ጥሩ ነው።
ይህን ጉዳይ አብራርቶ ማስረዳት አስፈላጊ መሆኑ በግል ያሸማቅቀኛል። የገንዘብ ስርአቱ በርካታ የተወሳሰቡ ችግሮች ያሉበት ሲሆን ችግሮቹ እዚህ እንዳብራራሁት ቀላል ቢሆኑ ጥራዝ የሚሞሉ መጸሃፍቶችን ባልጻፍኩ ነበር። የችግሮቹ ሁሉ ስርመሰረት ግን እዚህ እንደገለጽኩት ነው፤ የገንዘብ መጠን ሲጨምር የአንድ ገንዘብ አሃዝ መግዣ አቅሙን ያጣል። ኢንፍሌሽን የግል ጉዳያቸውን የሚረብሽባቸው ሰዎች የማይወዱት ይህን ሁኔታ ነው። የሚያማርሩት ከኢንፍሌሽን የማይጠቀሙት ሰዎች ናቸው።
ኢንፍሌሽን መጥፎ ከሆነ እና መጥፎነቱን ሰዎች ከተረዱት እንዴት ሁሉም ሀገራት ላይ የኑሮ ዘይቤ ሊሆን ቻለ? ሀብታም የሚባሉት ሀገራት ሳይቀር በዚህ በሽታ ተጠቅተዋል። የዛሬዋ አሜሪካ ዜጎቿ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው በአለም አንደኛ ሀብታም ሃገር ናት። ግን በአሜሪካ በሚጓዙበት ግዜ የዋጋ ግሽበትን እና እሱን የማስቆም አስፈላጊነት በተመለከተ የማያቋርጥ ወሬ እንዳለ ይገነዘባሉ። ወሬው ግን ከወሬነት አልፎ ወደ ተግባር አይቀየርም።
ኢንፍሌሽን እና የደመዎዝ መጠን
አንዳንድ እውንታዎችን ለመስጠት፤ የመጀመርያውን የአለም ጦርነት ተከትሎ ታላቋ ብሪታኒያ ወደ ቀድሞው የወርቅ ፓውንድ ተመለሰች። ማለትም የፓውንድን ዋጋ ከፍ አድርጋ ተመነች። ይህ ድርጊት የእያንዳንዱን ሰራተኛ ደሞዝ የመግዛት አቅም ጨመረ። የግዜው ገበያ ያልተገደበ ቢሆን ኖሮ ይህን ለውጥ ለማካካስ የሰራተኞች ደሞዝ የግዢ አቅሙ ሳይወርድ የደሞዝ መጠኑ ግን እንዲቀነስ ይፈቀድ ነበር(ደሞዛቸው ቢቀነስም በአዲሱ የገንዘብ ስርአት የትንሹ ደሞዝ የመግዣ አቅም በበፊቱ የገንዘብ ስርአት ከሚከፈለው ከፍ ያለ ደሞዝ እኩል ነው የሚሆነው)። ይህ የሚሆንበትን ምክንያት እዚህ ለማብራራት በቂ ግዜ የለንም። ነገር ግን የሀገሪቱ ገንዘብ መግዣ አቅም ሲጨምር የሚያስፈልገውን የደሞዝ ቅነሳ ማስተካከያ ለመቀበል የታላቋ ብሪታንያ የሰራተኞች ማህበራት ዝግጁ አልነበሩም። በዚህም ምክንያት የሰራተኛው የእውነተኛ ገቢ ጨምሮ ቀጠለ። ይህ ሁኔታ ለእንግሊዝ አስከፊ ነበር ምክንያቱም ታላቋ ብሪታንያ በዋነኝነት የኢንዱስትሪ መር ሀገር በመሆኗ እና ከውጭ ለምታስገባቸው ጥሬ እቃዎች፣ በከፊል ላለቁ ምርቶች እና ለመኖር ለሚያስፈልጓት ምግቦች ለመክፈል ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ ነበረባት። ፓውንድ በአለም ገበያ የሚገዛበት ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ የብሪታንያ ምርቶች ዋጋ በአለም ገበያ ጨመረ፤ የሽያጭ መጠን እና ከሀገር ውጭ የሚላከው የምርት መጠን ቀነሰ። ታላቋ ብሪታንያ ባስቀመጠችው ዋጋ በአለም ገበያ እራሷን ከገበያ ውድድር ውጭ አደረገች።
የሰራተኛ ማህበራት ሊሸነፉ አልቻሉም። በዛሬው ግዜ የሰራተኛ ማህበራት ያላቸው ሀይል ይታወቃል። የሀይል ጥቃት እሰከሚፈጽሙ ድረስ መብት አላቸው። የሰራተኛ ማህበር የሚያስተላልፈው ትእዛዝ ከመንግስት አዋጅ ያልተናነሰ አቅም አለው። የመንግስት አዋጅ የመንግስት አስፈጻሚ አካል(ፖሊስ) ሊያስፈጽመው ዝግጁ የሆነ ትእዛዝ ነው። የመንግስት አዋጅን አልቀበልም ያለ ሰው ከፖሊስ ችግር ይገጥመዋል።
አለመታደል ሁኖ አሁን አሁን በሁሉም ሀገር ማለት ይቻላል ኃይል መጠቀም የሚችል ሁለተኛ ኃይል አለ - የሰራተኛ ማህበራት። የሰራተኛ ማህበራት ደሞዝ ከወሰኑ በኋላ የስራ አመጽ በመጥራት አዲሱን የደሞዝ መጠን ለማጽናት ይታገላሉ። ስለ ሰራተኛ ማህበራት ጉዳይ አሁን በሰፊው አላወራም፣ በኋላ እመለስበታለሁ። ላስቀምጠው የፈለኩት ነገር የሰራተኛ ማህበራት ፖሊሲ የደሞዝ መጠንን ባልተገደበ ገበያ ከሚገኘው መጠን ከፍ እንዲል የሚያደርግ ነው። በዚህም ምክንያት ትንሽ የማይባል የሀገር የሰራተኛ ሀይል ቅጥር ሊያገኝ የሚችለው ኪሳራ ለማስተናገድ ዝግጁ ከሆኑ ሰዎች ወይም ኢንዱስትሪዎች ብቻ ነው። ድርጅቶች ደግሞ ኪሳራ እያስተናገዱ መቀጠል የማይችሉ በመሆናቸው በራቸውን ይዘጋሉ፣ የስራ አጥ ቁጥር ይጨምራል። የደሞዝ መጠንን ያልተገደበ ገበያ ከሚገኘው የደሞዝ መጠን ከፍ አድርጎ ማስቀመጥ ውጤቱ ሁሌም ከፍተኛ ስራ አጥነት መፍጠር ነው።
በታላቋ ብሪታንያ በሰራተኞች ማህበራት ተፈጻሚነት ያገኘው ከፍተኛ የደሞዝ መጠን ከአመት አመት የቀጠለ ዘላቂ ስራ አጥነት አስከትሏል። የምርት መጠን ሲያሽቆለቁል በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰራተኞች ስራ አጥ ሆነዋል። ይህ ሁኔታ ባለሙያዎችን እንኳ ግራ ያጋባ ነበር። በዚህ ሁኔታ ነው የብሪታንያ መንግስት አስፈላጊነቱ ግድ ነው ያለውን አስቸኳይ እርምጃ የተገበረው - የገንዘቡን ተመን መቀነስ።
ውጤቱ ሰራተኛ ማህበራት የታገሉለትን ደሞዝ መግዛት አቅሙን መሸርሸር ነበር። የይስሙላው ደሞዝ ባይቀንስም እውነተኛው ደሞዝ(ገንዘቡ የመግዛት አቅሙ በመዳከሙ) ቀነሰ። ምንም እንኳ የይስሙላው ደሞዝ ባይቀንስበትም ሰራተኛው በፊት በሚገዛበት መጠን አሁን መግዛት አልቻለም። በዚህ መንገድ እውነተኛው ደሞዝ መጠን ወደ ነጻ ገበያ ደረጃ ይጠጋል፣ ስራ አጥነትም ይጠፋል ተብሎ ታስቦ ነበር።
ይህ እርምጃ(የገንዘቡን አቅም ማዳከም) ፈረንሳይ፣ ሆላንድ እና ቤልጄምን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ተተግብሯል። አንድ ሀገር እንዳውም ይህን እርምጃ በአንድ አመት ከስድስት ወር ግዜ ውስጥ ሁለቴ ተገበረች። እቺ ሃገር ቼኮዝሎቫኪያ ናት። ይህ እርምጃ የሰራተኛ ማህበራትን ሀይል ለመቀልበስ የተደረገ ስውር እርምጃ ነው። ስኬታማ ነበር ለማለት ግን ያስቸግራል።
ከተወሰኑ አመታት በኋላ ሰራተኞቹ እና የሰራተኛ ማህበራቱ እየተፈጠረ ያለውን ነገር መረዳት ጀመሩ። የገንዘብ መግዣ አቅም መዳከም ደሞዛቸውን እንደሸረሸረው ተረዱ። ሰራተኛ ማህበራቱ ይህን ድርጊት የመቃወም ሀይል ነበራቸው። በብዙ ሀገሮች ውስጥ ደሞዝ ከኑሮ ውድነት ጋር አብሮ እንዲጨምር የሚደነግግ አንቀጽ በሰራተኞች ቅጥር ስምምነት ውል ውስጥ እንዲገባ ሰራተኛ ማህበራት አድረጉ። ይህ ኢንዴክሲንግ(Indexing) ይባላል። ሰራተኛ ማህበራት ስለ ኢንዴክሲንግ ተገነዘቡ። ስለዚህ ታላቋ ብሪታንያ እ.አ.አ በ1931 የጀመረቸው እና በሁሉም ተጠቃሽ መንግስታት ተከታይነት የተተገበረው ይህ ስውር ስራ አጥነትን መቀነሻ ዘዴ ዛሬ አይሰራም።
በሚያሳዝን ሁኔታ እ.አ.አ በ1936 General Theory of Employment, Interest and Money ብሎ ባሳተመው መጽሃፉ ጌታ ኬይንስ ይህን ዘዴ(እ.አ.አ ከ1929 እስከ 1933 በብሪታንያ የተተገበረውን አስቸኳይ ድንጋጌ) ወደ መርህ ደረጃ ከፍ በማድረግ እንደ መሰረታዊ የፖሊሲ ስርአት አቅርቦታል። እንዲህ ሲል አብራርቶታል፦ “ስራ አጥነት መጥፎ ነው። ስራ አጥነትን ለማስቀረት ገንዝቡን ኢንፍሌት ማድረግ አስፈላጊ ነው።”
ጌታ ኬይንስ የገበያው ደሞዝ መጠን ከሚገባው በላይ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል በሚገባ ተገንዝቧል። ማለትም የተቀመጠው የደሞዝ መጠን ከሙሉ ሰራተኛው ሀይል አንጻር አሰሪዎች ቅጥረኞች እንዳይጨምሩ የሚከለክል ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ተረድቷል። ምክንያቱም በሰራተኛ ማህበራት ተጽእኖ ከገበያው ደረጃ በላይ በተቀመጠ የደሞዝ መጠን ስርአት ከስራ ፈላጊው ህዝብ የተወሰነው ብቻ ነው ስራ ማግኘት የሚችለው።
ኬይንስም ከአመት አመት የሚንደረደር ከፍተኛ ስራ አጥነት አጥጋቢ ያልሆነ ሁኔታ እንደሆነ ተናግሯል። ነገር ግን የደሞዝ መጠን በገበያው መጠን ልክ መስተካከል እንደሚገባው እንደመናገር የሚከተለውን አይነት ነገር ሲናገር እናገኘዋለን፦ “የገንዘቡን አቅም ካዳከምነው እና ስለ ድርጊቱ ሰራተኞች ካልነቁ፣ የይስሙላ ደሞዛቸው እስካልቀነሰ እውነተኛ ደሞዛቸው መቀነሱን አውቀው አይቃወሙም።” በሌላ አገላለጽ የጌታ ኬይንስ አባባል፣ የአንድ ሰው ደሞዝ፣ ገንዘብ ከመውረዱ በፊት እና በኋላ ተመሳሳይ እስከሆነ ድረስ የገንዘቡ መግዣ አቅም መውረዱን እና አነስተኛ ተከፋይ መደረጉን አይጠረጥርም።
በድሮ ቋንቋ ከገለጽነው የጌታ ኬይንስ አስተያየት ሰራተኛውን እናጭበርብረው ነው። የደሞዝ መጠን በገበያው ሁኔታ መስተካከል እንዳለበት በግልጽ እንደማወጅ(ምክንያቱም ይህ ካልተደረገ የተወሰነው የሰራተኛ ሃይል ስራ አጥ ስለሚሆን) የጌታ ኬይንስ ሃሳብ እንደሚከተለው እንደማለት ነው፦”ሙሉ ቅጥረኝነት ላይ ልንደርስ የምንችለው በኢንፍሌሽን ብቻ ነው። ሰራተኞቹን እናታላቸው።” ነገር ግን ከሁሉም የሚያስገርመው እውነታ የጌታ ኬይንስ General Theory መጽሃፍ በመጨረሻ ለእትም ሲበቃ ይህን ማታለያ መተግበር አይቻልም ነበር። ምክንያቱም በዛ ግዜ ህዝቡ ስለ ኢንዴክሲንግ በቂ ግንዛቤ ፈጥሮ ነበር። የሙሉ ቅጥረኝነት ግብ ግን ቀጣይነትን አግኝቷል።
ደመዎዝ እና ሙሉ ቅጥረኝነት
“ሙሉ ቅጥረኝነት(full employment)” ምን ማለት ነው? ሀሳቡ ገደብ ከሌለው የቅጥር ገበያ ወይም በሰራተኛ ማህበራት እና በመንግስት ካልተረበሸ የቅጥር ገበያ ጋር ይያያዛል። ይህ የገበያ ስርአት በማንኛውም ስራ መስክ የተሰማራ ስራ ፈላጊ ሁሉ ስራ የሚያገኝበት እና ሁሉም ቀጣሪ በሚያስፈልገው የሰራተኛ መጠን ቅጥረኛ ይሚያገኝበት ነው። በቅጥረኞች ዘንድ ያለው ቅጥረኛ የማግኘት ፍላጎት ሲጨምር ለሰራተኛው የሚከፈለው ደሞዝ ከፍ የሚል ሲሆን ተፈላጊው የቅጥረኛ መጠን አነስተኛ ሲሆን የደሞዝ መጠን ዝቅ ይላል።
የ“ሙሉ ቅጥረኝነት” አይነት ሁኔታ ለማምጣት የሚያስችለው ብቸኛ መንገድ ያልተገደበ የቅጥር ገበያ ሲኖር ነው። ይህ ለይትኛውም አይነት ስራም ሆነ ምርት እውነት ነው።
የምርቱን አንድ አሀዝ በአምስት ዶላር መሸጥ የፈለገ ነጋዴ ምን ማድረግ ይችላል? በዛ ዋጋ መሸጥ ሲቸግረው በአሜሪካ ቢዝነስ ዘይቤያዊ አባባል “እቃው አይንቀሳቀስም(the inventory does not move)” ይባላል። ግን ግድ መንቀሳቀስ አለበት። ሽጦ አዲስ ነገር መግዛት ስላለበት እቃውን ይዞ መቀመጥ አይችልም። የሚሸጠው ነገር ፋሽንም እየተለወጠ ነው። ስለዚህ ዋጋውን ዝቅ አድርጎ ይሸጣል። 5 ዶላር መሸጥ ካቃተው በ4 መሸጥ ይኖርበታል። በ4 መሸጥ ካቃተው በ3 መሸጥ ይኖርበታል። ቢዝነስ ውስጥ ለመቆየት ሌላ አማራጭ የለውም። ኪሳራ ሊያጋጥመው ይችላል ግን የኪሳራው መንስኤ ስለምርቱ አዋጭነት የነበረው የተሳሳተ ግምት ነው።
በየአመቱ ገንዘብ ለማግኘት ከእርሻ ስፍራዎች በብዙ ሺዎች ወደ ከተማ ለሚፈልሱት ወጣቶች ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በሁሉም ኢንዱስትሪያል ሃገር አንድ አይነት ታሪክ ነው። አሜሪካ ውስጥ ለምሳሌ በሳምንት 100ዶላር እንሰራለን ብለው ይመጣሉ። ይህ ግን የማይሆን ነው። ስለዚህ አንድ ሰው በ100 ዶላር ስራ ማግኘት ካልቻለ በ90 ወይም በ80 ምናልባትም ከዛም ዝቅ ባለ ገንዘብ ስራ ለማግኘት መሞከር ይኖርበታል። ነገር ግን እንደ ሰራተኛ ማህበራቱ “100 ዶላር ወይም ምንም” የሚል አቋም ካለው በስራ አጥነቱ የመቀጠል ሰፊ እድል አለው(መንግስት ከቀጣሪዎች በሰበሰበው ግብር የስራ አጥ ድጎማ ስለሚከፍላቸው ስራ አጥ መሆን የማይረብሻቸው ብዙ ሰዎች አሉ። አንዳንዴ ይህ ድጎማ ሰዎቹ ሰርተው ሊያገኙ ከሚችሉት ገንዘብ የላቀ ይሆናል)።
የተወሰኑ ሰዎች ሙሉ ቅጥረኝነት ሊገኝ የሚችለው በኢንፍሌሽን ብቻ ነው ብለው ስለሚያስቡ በአሜሪካ ኢንፍሌሽን ተቀባይነት አግኝቷል። ግን ሰዎች የሚወያዩበት ጥያቄ ሆኗል፦ አስተማማኝ ገንዘብ ከስራ አጥነት ጋር ይኑር ወይስ ከኢንፍሌሽን ጋር ሙሉ ቅጥረኝነት? ይህ ግን አደጋ የተጋረጠበት ትንተና ነው።
ይህን ችግር ለመፍታት የሚከተለውን ጥያቄ መጠየቅ አለብን፦ የሰራተኞችንም ሆነ የመላውን ማህበረሰብ ህይወት እንዴት ማሻሻል ይቻላል? የዚህም መልስ እንደሚከተለው ነው፦ ባልተገደበ የቅጥር ገበያ ሙሉ ቅጥረኝነትን እውን በማድረግ። ከፊታችን የተጋረጠው ጥያቄ፣ ገበያው የደሞዝ መጠነን ይወስን ወይስ ደሞዝ በሰራተኛ ማህበር ጫና እና በአስገዳጅነት ይወሰን የሚል ነው እንጂ ከኢንፍሌሽን እና ከስራ አጥነት የቱን እንምረጥ አይደለም።
ይህ የተሳሳት ትንተና በእንግሊዝ፣ በአውሮፓ ሃገራት እንዲሁም በአሜሪካ እንደ መከራከርያ ነጥብ ይነሳል። አንዳንድ ሰዎች እንደሚከተለው ሲሉ ይሰማል፦ “አሜሪካ እንኳ ኢንፍሌት እያረገች ነው። እኛስ ለምን አናደርግም።”
ለነዚህ ሰዎች የመጀመርያ መልስ መሆን ያለበት፦ “ሀብታም ሰው ካለው ቅንጦት መሀከል አንዱ ከድሃ ሰው በጣም ረዘም ላለ ግዜ ሞኝ መሆን መቻሉ ነው።” አሜሪካ ያለችበት ሁኔታ ይህ ነው። የአሜሪካ የገንዘብ ፖሊሲ በጣም መጥፎ እና እየተባባሰ ያለ ነው። ምናልባት አሜሪካ ከሌሎች ሀገራት አንጻር ረዘም ላለ ግዜ ሞኝ ሁና መቀጠል ትችል ይሆናል።
ከሁሉም በላይ መታወስ ያለበት ነገር ኢንፍሌሽን የፈጣሪ ተግባር አለመሆኑ ነው። ኢንፍሌሽን የተፈጥሮ ቁጣም ሆነ እንደ በሽታ ወረርሽኝ በራሱ የሚነሳ ነገር አይደለም። ኢንፍሌሽን ፖሊሲ ነው። ከስራ አጥነት ይሻላል ብለው በሚያስቡ ሰዎች ሆን ተብሎ የሚተገበር ፖሊሲ ነው። እውነታው ግን ኢንፍሌሽን በአጭሩ ሩጫም ቢሆን ስራ አጥነትን አይቀርፍም።
ኢንፍሌሽን ፖሊሲ ነው። ፖሊሲ ደግሞ መቀየር ይችላል። ለኢንፍሌሽን እጅ የምንሰጥበት ምንም ምክንያት የለም። ኢንፍሌሽን በማህበረሰቡ እንደ ክፋት ከታየ ማስቆም ይቻላል። እርግጥ የመንግስት በጀትን ማመጣጠን አስፈላጊ ነው። ይህንንም ለማድረግ የህዝብ ድጋፍ ይጠይቃል፤ ምሁንራንም ህዝብ እንዲረዳ የበኩላቸውን ማድረግ አለባቸው። የህዝብ ድጋፍ ካለ የህዝብ ተወካዮች ኢንፍሌሽንን ማቆም ይችላሉ።
ምንም እንኳ በረጅሙ እይታ ሁላችንም ሟች ብንሆንም ማስታወስ ያለብን ነገር በአጭሩ ግዜ እይታ የምድር አኗኗራችንን የማስተካከል እና አሻሽሎ የመቀየስ ግዴታ እንዳለብን ነው። ይህንንም አላማ ለማሳካት አስፈላጊ ከሆኑት እርምጃዎች አንዱ የኢንፍሌሽን ፖሊሲን ጥሎ መሄድ ነው።