ጣልቃ ገብነት
አንድ ብዙ ግዜ የሚጠቀስ ታዋቂ አባባል አለ:- “ከሁሉም የሚሻለው መንግስት በትንሹ የሚያስተዳድረው ነው።” ይህ ስለ ጥሩ መንግስት ተግባራት ትክክለኛ መግለጫ ነው ብዬ አላምንም። መንግስት በሚያስፈልግበት ደረጃ ስራውን ማከናወን እና የተቋቋመበትን ተልዕኮ መወጣት አለበት። መንግስት የሀገሪቱን ህዝብ በወሮበሎች ከሚሰነዘሩ የሀይል እና የማጭበርበር ጥቃቶች መከላከል አለበት። ከዛም አልፎ ሀገሪቱን ከውጭ ጥቃት መጠበቅ አለበት። በነጻ ስርዓት በገበያ መር ኢኮኖሚ ስር የመንግስት ስራዎች እነዚህ ናቸው።
በእርግጥ በሶሻሊዝም ስር መንግስት ሙሉ በሙሉ አምባገነን የሆነበት ሲሆን ከመንግስት ቁጥጥር እና ስልጣን ውጭ የሆነ ነገር የለም። በአንጻሩ በገበያ መር ስርዓት ስር የመንግስት ዋና ስራ የገበያውን ኢኮኖሚ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ከመጡ አጭበርባሪዎች እና ጥቃት አራማጆች መጠበቅ ነው።
በዚህ የመንግስት ተግባር ፍች የማይስማሙ ሰዎች “ይህ ሰው መንግስትን ይጠላል” ሊሉ ይችላሉ። ይህ መልስ ግን ከእውነት የራቀ ነው። ቤንዚን በጣም ጠቃሚ ፈሳሽ እንደሆነ እና ለብዙ ጥቅሞች እንደሚውል ከተናገርኩ በኋላ ለመጠጥ ተገቢ ፈሳሽ ባለመሆኑ አልጠጣውም ብል የቤንዚን ጠላት ነኝ ማለት አይደለም፤ ቤንዚንን የሚጠላ ሰው ልባልም አልችልም። ተናግሬዋለሁ ሊባል የሚችል ነገር ቢኖር ቤንዚን ለአንዳንድ ጥቅሞች ተገቢ እንደሆነ እና ለሌሎች ጥቅሞች ደግሞ ተገቢ እንዳልሆነ ነው። የመንግስት ተልእኮ ነፍሰገዳዮችን እና ሌሎች ወንጀለኞችን ማሰር እንጂ የባቡር መስመሮችን ማስተዳደር ወይም የማይረቡ ነገሮች ላይ ገንዘብ ማባከን አይደለም ብል መንግስት ጠል ሊያስብለኝ አይችልም። መንግስት አንዳንድ ነገሮችን የማከናወን ብቃት ያለው እና ሌሎች ነገሮችን የማከናወን ብቃት የሌለው ተቋም ነው ማለት የመንግስት ጠላት ሊያስብል አይችልም።
በአሁኑ ዘመን የነጻ ኢኮኖሚ ስርዓትን ጠብቀን መራመድ አቁመናል ይባላል። ያለንበት ዘመን “የድብልቅ ኢኮኖሚ” ዘመን ይባላል። ይህንንም ለማሳየት በመንግስት ባለቤትነት እና ቁጥጥር ስር ወደዋሉት በርካታ ድርጅቶች ሰዎች እንደመረጃ ይጠቁማሉ። በብዙ ሀገሮች ውስጥ የቴሌቭዥን፣ የቴሌግራፍ፣ የባቡር እና የመሳሰሉ ተቋማት በመንግስት ባለቤትነት የሚተዳደሩ በመሆናቸው ኢኮኖሚው የድብልቅ ኢኮኖሚ ነው ይባላል።
በመንግስት የሚተዳደሩ ድርጅቶች
ከነዚህ ተቋማት እና ድርጅቶች መካከል የተወሰኑት በመንግስት የሚተዳደሩ መሆናቸው በእርግጥ እውነት ነው። ነገር ግን ይህ እውነታ ብቻውን የኢኮኖሚ ስርዓቱን ገጽታ አይቀይረውም። በሌላው ረገድ ሶሻሊስት ባልሆነው ነጻ ገበያ ውስጥ “ትንሽ ሶሻሊዝም” ተፈጥሯል ማለት እንኳን አንችልም። ምክንያቱም መንግስት እነዚህን ድርጅቶች በሚያስተዳድርበት ሂደት ለገበያው የበላይነት ተገዢ ነው፤ ይህ ማለት ደግሞ ለሸማቹ የበላይነት ተገዢ ነው ማለት ነው። መንግስት ለምሳሌ ፖስታ ቤት እና ባቡር በሚያስተዳድርበት ሁኔታ እነዚህ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችን መቅጠር ይኖርበታል። ድርጅቶቹን ለማስተዳደር የሚያስፈልገውን ጥሬ እቃ እና ሌሎች ቁሶችን መግዛት ይኖርበታል። በሌላ በኩል ደግሞ በነዚህ ድርጅቶች አማካኝነት አገልግሎቶችን እና ምርቶችን ይሸጣል። ነገር ግን ምንም እንኳ መንግስት እነዚህን ድርጅቶች የሚያስተዳድረው የነጻውን ገበያ መንገድ በመጠቀም ቢሆንም አብዛኛውን ግዜ ውጤቱ ኪሳራ ነው። ነገር ግን መንግስት ይህንን ኪሳራ መሸፈን የሚችልበት ቦታ ላይ ይገኛል(ቢያንስ የመንግስት አባላት እና የመሪው ፓርቲ አባላት ይህንን ያምናሉ)።
ለግለሰብ ግን ሁኔታው በእርግጠኝነት የተለየ ነው። የአንድ ግለሰብ በኪሳራ የመቀጠል አቅም በጣም ውስን ነው። ኪሳራ በአጭር ግዜ ውስጥ ቁሞ ድርጅቱ አትራፊ መሆን ካልጀመረ(ወይም ተጨማሪ ኪሳራ መፈጠሩ ካልቆመ) ግለሰቡ ሙሉ በሙሉ ይከስርና ድርጅቱ ፍጻሜውን ያገኛል።
ለመንግስት ግን ሁኔታው የተለየ ነው። መንግስት ሰዎች ላይ ግብር የመጣል ስልጣን ስላለው በኪሳራ መቀጠል ይችላል። መንግስት ድርጅቶችን በኪሳራ ይዞ እንዲቀጥል(ማለትም ከግል ተቋም አንጻር በአነሳ ብቃት እና ቅልጥፍና እያስተዳደረ እንዲቀጥል) ለማስቻል ግብር ከፋዮች ከፍተኛ ግብር ለመክፈል ዝግጁ ከሆኑ እና ኪሳራ ተቀባይ ከሆኑ ድርጅቶችን በኪሳራ ማስቀጠል ይቻላል።
በቅርብ አመታት የብዙ ሀገራት መንግስታት የብሄራዊ ኢንዱስትሪ እና ድርጅቶችን ብዛት ከመጨመራቸው የተነሳ የሚመዘገበው የኪሳራ መጠን ከህዝብ በግብር ከሚሰበሰበው ገንዘብ መጠን በላይ ሆኗል። ይህንን ተከትሎ ስለሚፈጠረው ነገር የዛሬው ንግግር ርዕሰ ጉዳይ አይደለም። ውጤቱ ኢንፍሌሽን ሲሆን ነገ በማደርገው ንግግር አብራራለሁ። ይህንን ያነሳሁብበት ምክንያት ድብልቅ ኢኮኖሚ የዛሬው ርዕሰ ጉዳይ ከሆነው ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ችግር ጋር መምታታት ስለሌለበት ነው።
ጣልቃ ገብነት ምንድን ነው
ጣልቃ ገብነት ምንድን ነው? ጣልቃ ገብነት ማለት የማህበረሰብ ስርዓትን ጠብቆ ለማስቀጠል በሚያደርገው ስራ ያልተገደበ የመንግስት ስርዓት ነው። ወይም ከመቶ አመት በፊት የነበሩ ሰዎች እንደሚሉት “ከጥበቃ አምራችነት" የዘለለ ስራ የሚከውን መንግስት ነው። ጣልቃ ገብነት ማለት መንግስት ተጨማሪ ስራዎችን መከወን የሚፈልግበት ነው። በገበያው ስርዓት ጣልቃ መግባት ይፈልጋል።
አንድ ሰው ይህን ጣልቃ ገብነት በመቃወም መንግስት ከንግድ ስርዓቱ እጁን ማንሳት አለበት ሲል ከብዙ ሰዎች የሚከተለውን ምላሽ ያገኛል፡ “መንግስት ሁሌም ጣልቃ መግባት አለበት። መንገድ ላይ የህግ አስከባሪዎች ያሉት በመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው። ሱቆች በሌባ የማይዘረፉት በመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው። መኪና በሌባ የማይዘረፈው በመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው።” ነገር ግን እኛ እዚህ ስለ ጣልቃ ገብነት ስናነሳ መንግስት በገበያው ስርዓት ስለሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ነው።(ነጋዴውንም ሆነ ማንኛውንም ዜጋ በሃገር በቀል ሆነ የውጭ ወንበዴ ከሚደረግ ጥቃት የመከላከል ስራ የማንኛውም መንግስት መደበኛ እና አስፈላጊ ተልዕኮ ነው። የዚህ አይነት ጥበቃ ጣልቃ ገብነት አይደለም ምክንያቱም የመንግስት ብቸኛው ተገቢ ተልዕኮ የጥበቃ ምርት ነው።
ስለ ጣልቃ ገብነት ስናነሳ እያወራን ያለነው መንግስት ጥቃት እና ማጭበርበርን ከመከላከል በዘለለ ሊሰራቸው ስለሚፈልገው ተግባራት ነው። ጣልቃ ገብነት ማለት መንግስት የገበያው ስርዓት በተለሳለሰ ስርዓት እንዲከናወን ተገቢውን ከለላ ካለመስጠትም በተጨማሪ በተለያዩ የገበያ ክንውኖች እጁን የሚያስገባበት ነው። በገበያ ዋጋ እጁን የሚያስገባበት፣ በደመዎዝ ዋጋ፣ በወለድ እና በትርፍ መጠን ጣልቃ የሚገባበት።
የነጋዴው ብቸኛ አለቃ በሆነበት ግዜ ነጋዴው ስራውን ከሚከውንበት መንገድ በተለየ ሁኔታ ስራውን እንዲሰራ መንግስት ማስገደድ ይፈልጋል። በመሆኑም እያንዳንዱ የመንግስት ጣልቃገብ እርምጃ የሸማቹን የበላይነት የሚቀናቀን ነው። በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ በሸማች እጅ ስር የሆነውን ስልጣን መንግስት በከፊል ወይንም ሙሉ በሙሉ ወደራሱ ማምጣት ይፈልጋል።
አንድ የጣልቃ ገብነት ምሳሌ እናንሳ። ይህ እርምጃ በብዙ ሀገራት ተወዳጅ የሆነ እና በብዙ መንግስታት በተለይ በኢንፍሌሽን ወቅት በተደጋጋሚ የተሞከረ እርምጃ ነው። እሱም የዋጋ ትመና ነው።
ብዙ ግዜ መንግስታት ወደ ዋጋ ቁጥጥር የሚሄዱት የሀገሪቱን የገንዘብ መጠን ኢንፍሌት ካደረጉ በኋላ በሚከተለው የዋጋ ግሽበት ሰው መማረር ሲጀምር ነው። በታሪክ በርካታ ታዋቂ የከሸፉ የዋጋ ቁጥጥር ምሳሌዎች ያሉ ሲሆን መንግስት ዋጋ ተመኑን በከፍተኛ ጥረት ሊያስፈጽም ከሞከረበት ምሳሌዎች ሁለቱን እንጥቀስ።
የመጀመርያው ታዋቂ ምሳሌ የሮማን ንጉሰ ነገስት የነበረውና የክርስትያን ሃይማኖት ተከታዮችን በማጥቃት ከሚታወቁት የሮማን ንጉሰ ነገስታት የመጨረሻ የነበረው ዳዮክሊሻን ነው። ይህ የሮማን ንጉሰ ነገስት በሶስተኛው ክፍለዘመን ሁለተኛ ክፍል አንድ የፋይናንስ አማራጭ ብቻ ነበረው። እሱም ምንዛሬውን ማራከስ። በዚህ ማተምያ ቤት ባልተፈጠረበት ኋላ ቀር ዘመን ኢንፍሌሽንም መፍጠር የሚቻለው በኋላ ቀር መንገድ ነበር። በግዜው ገንዘብ የነበረውን የብር ሳንቲም በማራከስ። የግዜው መንግስት ከግዜ ወደ ግዜ ተጨማሪ የመዳብ ንጥረ ነገር ከብር ጋር መቀላቀል ጀመረ። በሂደት ገንዘብ የነበረው የብር ሳንቲም ቀለሙን ቀየረ፣ ክብደቱም ቀላል በማይባል ደረጃ ቀነሰ። የዚህ የገንዘብ ማራከስ እርምጃ እና ውጤቱ የሆነው የአጠቃላይ የገንዘብ ብዛት መጨመር የዋጋ ጭማሪን አስከተለ። ይህንንም ተከትሎ የዋጋ ቁጥጥር አዋጅ ታወጀ። የሮማን ንጉሰ ነገስታት ይህንን አዋጅ ሲተገብሩ በተለሳለሰ መንገድ አልነበረም። ዋጋ ጨምሮ የተናገረ ሰው ላይ የሞት ፍርድ ከመፍረድ ወደኋላ አይሉም ነበር። ዋጋ ትመናን ማስፈጸም የቻሉ ቢሆንም ማህበረሰቡን ጠብቀው ማቆየት ተሳናቸው። ውጤቱም የስራ ክፍፍል ስርዓቱ እና የሚያስተዳድሩት ግዛት መበታተን ነበር።
ከዛም ከአንድ ሺህ አምስት መቶ አመታት በኋላ ተመሳሳይ የገንዘብ ማራከስ እርምጃ በፈረንሳይ አብዮት ወቅት ተፈጽሟል። በዚህ ግዜ ግን በተለየ መንገድ ነበር። ገንዘብ የሚመረትበት ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ደረጃ የተሻሻለበት ግዜ ነበር። ፈረንሳውያን ለገንዘብ የሚጠቀሙበት ሳንቲም ላይ ባዕድ ነገር መቀላቀል አልነበረባቸውም ምክንያቱም የገንዘብ ማተምያ ነበራቸው። የማተምያ መሳሪያቸውም ፈጣን እና ውጤታማ ነበር። በድጋሜ ውጤቱ ታይቶ የማይታወቅ የዋጋ ግሽበት አስከተለ። ምንም እንኳ በፈረንሳይ አብዮት ወቅት የዋጋ ጣሪያ አዋጅን መተላለፍ ቅጣቱ ልክ እንደ ዳዮክሊሻን ግዛት ዘመን የሞት ፍርድ ቢሆንም ሰው የሚገደልበት መንገድ ተቀይሮ ነበር። ጊሎቲን ጥቅም ላይ እንዲውል ሲገፋ ስለነበረው ታዋቂ ዶክተር “ጄ አይ ጊሎቲን" ሁላችንም እናውቃለን። ነገር ግን ምንም እንኳ ጊሎቲን ጥቅም ላይ የዋለ ቢሆንም የዋጋ ጣሪያ አዋጁን ከመክሸፍ አላዳነውም። ሮበስፒር እራሱ ወደ በጊሎቲን ወደሚገደልበት ሲያመራ ህዝቡ “ይህ ቆሻሻ ጣርያ ሲሄድ ተመልከቱ" በማለት ሲጮህ ይሰማ ነበር።
ይህንን መጥቀስ የፈለኩት ምክንያት ብዙ ግዜ ሰዎች እንደሚከተለው ሲናገሩ ስለሚሰሙ ነው - “ዋጋ ተመኑ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስፈልገው ተጨማሪ እና ጎምዘዝ ያለ እርምጃ ነው።” ዳዮክሊሻን እና የፈረንሳይ አብዮት፣ ሁለቱም በእርግጠኝነት ጭካኔ የተሞሉ ነበሩ። ቢሆንም ግን የዋጋ ተመን በሁለቱም ዘመን ሙሉ በሙሉ ስኬት አልባ ነበር።
ዋጋ ቁጥጥር የሚከሽፍበት ምክንያት
አሁን ለዚህ ክሽፈት ምክንያት የሆኑትን ነገሮች እንመልከት። ሰዎች በወተት ዋጋ መጨመር ሲማረሩ መንግስት ይሰማል። እርግጥ ነው ወተት በተለይ ለታዳጊዎች አስፈላጊ ነገር ነው። ይህንንም ተከትሎ መንግስት ከገበያ ዋጋ ዝቅ ባለ ዋጋ ለወተት የዋጋ ጣርያ ያስቀምጣል። አሁን መንግስት እንደሚከተለው ይናገራል፡ “ድሃ ወላጆች ለልጆቻቸው በሚያስፈልጋቸው ደረጃ ወተት እንዲገዙ የተቻለንን አድርገናል።”
አሁን ምን ይፈጠራል። በአንድ በኩል በመንግስት የተተመነው ዝቅ ያለ ዋጋ የወተት ፍላጎትን ይጨምራል። ከፍ ባለ ዋጋ ወተት መግዛት የማይችሉ ሰዎች መንግስት ባስቀመጠው ዋጋ መግዛት ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከፍ ባለ ወጪ ወተትን የሚያመርቱ አምራቾች(ማርጂናል አምራቾች) ኪሳራ ይገጥማቸዋል ምክንያቱም መንግስት ያስቀመጠው ዋጋ ከወጪያቸው ያንሳል። የገበያ ኢኮኖሚ ዋና ጭብጡ እዚህ ላይ ነው። የግል አምራቹ ለረጅም ግዜ ኪሳራ እያስተናገደ መቀጠል አይችልም። በወተት ምርት መክሰር ስለማይፈልግ የወተት ምርቱን ይቀንሳል። የተወሰኑ ላሞቹን ለእርድ ይሸጣል ወይም ወተት ከማምረት ይልቅ ክሬም፣ ቅቤ እና አይብ የመሳሰሉ የወተት ተዋጽኦ ምርቶችን መሸጥ ይጀምራል።
ስለዚህ መንግስት በወተት ዋጋ ላይ የፈጠረው ጣልቃ ገብነት የወተት ምርት በፊት ከነበረው እንዲቀንስ እንዲሁም በተመሳሳይ ግዜ የወተት ፍላጎት እንዲጨምር ያደርጋል። አንዳንድ በመንግስት ዋጋ ወተት ለመግዛት የሚሞክሩ ሰዎች ወተት ማግኘት ያቅታቸዋል። ሌላው ውጤት ወተት ለመግዛት የጓጉ ሰዎች ሱቅ ቀድመው ሄደው መሰለፍ ነው። ውጭ ቆመው ይጠብቃሉ። ሱቅ ፊት የሚታይ ረጅም የሰው ሰልፍ ሁሌም መንግስት አስፈላጊ ብሎ የዋጋ ጣርያ የተመነባቸውን ምርቶች ለማግኘት ከሚደረግ ጥረት የመነጨ ክስተት ነው። ይህ ክስተት የወተት ዋጋ በተተመነበት ግዜ በሙሉ የተፈጠረ ነው። ይህ ክስተት ሁሌም በኢኮኖሚስቶች የሚተነበይ ነው። ያው ደህና በሚባሉ ኢኮኖሚስቶች። የነሱም ቁጥር ትልቅ የሚባል አይደለም።
ነገር ግን የመንግስት ዋጋ ቁጥጥር ፋይዳ ምንድን ነው። መንግስት የሚፈልገውን ውጤት አያገኝበትም። የወተት ተጠቃሚዎችን ፍላጎት ማርካት ይፈልጋል። በድርጊቱ ግን ይበልጥ ቅር አሰኝቷቸዋል። መንግስት እጁን ከማስገባቱ በፊት የወተት ዋጋ ውድ ቢሆንም ገበያ ላይ ይገኝ ነበር። አሁን ግን በቂ ወተት የለም። በዚህም ምክንያት አጠቃላይ የወተት ፍጆታ ይቀንሳል። ልጆች የሚያገኙት የወተት መጠን ይቀንሳል እንጅ አይጨምርም። ይህንንም ተከትሎ መንግስት ብቸኛ አማራጭ ብሎ ወደሚያስበው ራሽን ወደማድረግ ይሄዳል። ራሽን ማለት ግን የተወሰኑ ባለ ልዩ መብቶች ወተት የሚያገኙበት እና ሌሎች ሰዎች ጭራሽ ምንም የማያገኙበት ስርዓት ነው። ወተት የሚያገኘው እና የማያገኘው ሰው በዘፈቀደ የሚወሰንበት ስርዓት ነው። አንድ የራሽን ምሳሌ ከአራት አመት በታች ለሆኑ ልጆች በቂ ወተት የሚመደብበት እና እድሜያቸው ከአራት አመት በላይ ወይም እድሜያቸው ከአራት እስከ ስድስት አመት ለሆኑ ልጆች ደግሞ አራት አመት ላልሆናቸው ከተመደበው ግማሽ ያህል የሚመደብበት ስርዓት ይሆናል።
መንግስት የትኛውንም አይነት አመዳደብ ቢከተል እየወረደ ያለውን የወተት አቅርቦት እውነታ መቀየር አይችልም። በዚህም ምክንያት ሰዎች ከበፊቱ ይበልጥ እርካታ ያጣሉ። ይህንንም ተከትሎ መንግስት የሚከተለውን ጥያቄ ለወተት አምራቾች ያቀርባል፡ “ወተት በፊት በምታመርቱበት መጠን ለምን አታመርቱም?” መንግስት የሚከተለውን መልስ ያገኛል። “የምርት ፍጆታ ዋጋ መንግስት ካስቀመጠው የዋጋ ጣሪያ በላይ በመሆኑ አልቻልንም።” መንግስት የወተት ምርት ግብዓት የሆኑ ንጥረ ነገሮች እና ዋጋቸው ላይ ጥናት ያካሄድና አንዱ ንጥረ ነገር መኖ መሆኑን ይረዳል።
“አሃ” ይላል መንግስት “ወተት ላይ የጣልነውን የዋጋ ቁጥጥር መኖ ላይ እንደግመዋለን። ለመኖም የዋጋ ጣሪያ በመደንገግ ላሞቻችሁን በዝቅተኛ ዋጋ እና ወጪ መመገብ ትችላላቹ። ይህንንም ተከትሎ ሁሉም ነገር ይስተካከላል። ተጨማሪ ወተት ማምረት እና መሸጥ ትችላላቹህ።”
ግን አሁን ምን ይሆናል? በተመሳሳይ ምክንያት የወተት ታሪክ መኖ ላይ ይደገማል። የመኖ ምርት ይቀንስና መንግስት በድጋሜ ተመሳሳይ አጣብቂኝ ተደቅኖበት ያገኛል። ስለዚህ መንግስት የመኖ ምርት እንቆቅልሽን ለመፍታት ሌላ አዲስ ችሎት ያካሄዳል። እናም ከወተት አምራቾች ያገኘውን ተመሳሳይ መልስ ከመኖ አምራቾች ያገኛል። ይህንንም ተከትሎ ለመኖ ግብዓት የሆኑ ምርቶች ላይ የዋጋ ጣሪያ ይተምናል። ታሪክ እራሱን ይደግማል።
በተመሳሳይ ግዜ መንግስት ወተትን ብቻ ሳይሆን እንቁላል፣ ስጋ እና ሌሎች ምርቶችን መቆጣጠር ይጀምራል። እና መንግስት ተመሳሳይ ውጤት ባገኘ ቁጥር በሁሉም ቦታ መዘዙ አንድ ነው። መንግስት አንዴ የሸማች ምርቶች ላይ የዋጋ ጣሪያ ሲያስቀምጥ ወደ ኋሏ ተመልሶ ለነሱ ግብዓት የሆኑ የአምራች ምርቶችን ዋጋ መቆጣጠር አለበት። እናም መንግስት ከውስን ዋጋ ቁጥጥር ቢነሳም በምርቱ ሂደት ወደ ኋሏ እያፈገፈገ በብዙ የአምራች ምርቶች ላይ የዋጋ ጣሪያ እየወሰነ ይሄዳል። ይህ ውሳኔ በሂደት የሰራተኛ ዋጋን ጨምሮ ያጠቃልላል፣ ምክንያቱም ያለ ደመዎዝ ቁጥጥር የመንግስት “ዋጋ ቁጥጥር” ትርጉም የለሽ ይሆናል።
ከዚህም በላይ መንግሥት በገበያው ውስጥ የሚያደርገውን ጣልቃገብነት እንደ ወተት፣ ቅቤ፣ እንቁላል እና ሥጋ ባሉ አስፈላጊ ነገሮች ላይ ብቻ ሊገድበው አይችልም። የግድ የቅንጦት ዕቃዎችን ማካተት አለበት ምክንያቱም የነሱም ዋጋ ካልተገደበ ካፒታል እና ጉልበት የአስፈላጊ ሸቀጦችን ምርት ጥሎ መንግስት ቅንጦት እና አላስፈላጊ ብሎ ወደፈረጃቸው ምርቶች ይሄዳል። ስለዚህ በአንድ ወይም በጥቂት የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የተጣለው ውስን ጣልቃገብነት በፊት ከነበረው ሁኔታ አጥጋቢነቱ የወረደ ውጤት ይዞ ይከተላል።
መንግሥት ጣልቃ ከመግባቱ በፊት ወተት እና እንቁላል ውድ ነበሩ; መንግሥት ጣልቃ ከገባ በኋላ ከገበያ መጥፋት ጀመሩ። መንግስት እነዚህ ሸቀጦች በጣም አስፈላጊ አድርጎ ከመቁጠሩ የተነሳ ምርቱን ለመጨመር እና አቅርቦቱን ለማሻሻል ፈልጎ ጣልቃ ገብቷል። ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ሆነ። ውስን ጣልቃገብነት በመንግስት እይታ ራሱ ቀድሞ ሊቀይረው ከፈለገው ሁኔታ የሚብስ ሁኔታ ፈጠረ። እናም መንግስት በዚህ መንገድ ረጅም ርቀት ሲጓዝ በመጨረሻ ሁሉም የምርት ዋጋ፣ ሁሉም የደመዎዝ መጠን፣ ሁሉም የወለድ መጠን፣ በአጭሩ በመላው የኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ነገር በመንግስት የሚወሰንበት ደረጃ ይደርሳል። ይሄም በግልጽ ሶሻሊዝም ነው።
እዚህ የተናገርኩት ነገር፣ ይህ የንድፈ ሃሳብ እና ንድፈ ሃሳባዊ ማብራሪያ፣ በሃገራቸው እስከ መጨረሻው ከፍተኛ ዋጋ ቁጥጥርን ደረጃ በደረጃ እና በግትርነት ለማስፈጸም በሞከሩ መንግስታት አማካኝነት የተከሰተውን ነው። ይህ ሁኔታ በአንደኛው የዓለም ጦርነት በጀርመን እና በእንግሊዝ ተከስቷል።
የጦርነት ግዜ ጣልቃገብነቶች
በሁለቱም አገሮች ያለውን ሁኔታ እንመርምር:: ሁለቱም ሀገሮች ኢንፍሌሽን አጋጥሟቸዋል። ዋጋ በመናሩ ሁለቱም መንግስታት የዋጋ ቁጥጥር ጣሉ። ወተት እና እንቁላልን ጨምሮ ከተወሰኑ ዋጋዎች ጀምረው እየገፉ እየገፉ መሄድ ነበረባቸው። ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር ኢንፍሌሽን በዛው ልክ እየጨመረ ሄደ። እና ከሶስት አመታት ጦርነት በሁአላ ጀርመኖች – እንደ ሁልግዜው በስልታቸው – ታላቅ እቅድ አወጡ። የሂንደንበርግ እቅድ ብለው ሰየሙት፡ በግዜው በጀርመን መንግስት ጥሩ ነገር ተብሎ የሚታሰብ ነገር ሁሉ የሂንደንበርግ ስያሜ ተሰጠው።
የሂንደንበርግ እቅድ ፋይዳው አጠቃላይ የጀርመን የኢኮኖሚ ስርዓት በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲውል የሚያደርግ ነበር፤ ዋጋዎች፣ ደመዎዝ፣ ትርፍ… ሁሉም ነገር። እና ቢሮክራሲው ወድያውኑ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ። ነገር ግን ሳይጨርሱ ትልቅ ድባቅ መጣ፤ የጀርመን ንጉሠ ነገሥት ፈራረሰ፣ አጠቃላይ ቢሮክራሴው ጠፋ፣ አብዮቱ ደም አፋሳሽ ውጤት አስከተለ – ነገሮች አበቁ።
በእንግሊዝ ነገሮች በተመሳሳይ መንገድ ቢጀምሩም እ.ዓ.ዓ በ1917 ዓ.ም በጸደይ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ጦርነቱ ገብታ ለእንግሊዝ በቂ ምርት ማቅረብ ጀመረች። ስለዚህ የሶሻሊዝም መንገድ፣ ወደ ባርነት የሚወስደው መንገድ ተቋረጠ።
ሂትለር ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት ቻንስለር ብሩኒንግ በተለመዱት ምክንያቶች በጀርመን የዋጋ ቁጥጥር በድጋሜ እንዲጀመር አደረገ። ሂትለር ስልጣን ከመጣም በኋላ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ቁጥጥሩን ቀጥሎበት ነበር። ምክንያቱም በሂትለር ጀርመን ውስጥ የግል ድርጅት ወይም የግል ተነሳሽነት አልነበረም። በሂትለር ጀርመን ስር የነበረው የሶሻሊዝም ሥርዓት ከሩሲያው ስርዓት ይለይ የነበረው የነጻ ኢኮኖሚ ቃላቶች በስያሜ ደረጃ በመቀጠላቸው ነው። “የግል ድርጅት" የሚል ስያሜ ያላቸው ተቋማት ነበሩ። ባለቤቶቹ ግን በባለቤትነት ሳይሆን የሚታወቁት “የሱቅ ስራ አስኪያጅ”(Betriebsführer) በሚል ስያሜ ነበር።
መላው ጀርመን በፉህረር (führer) ተዋረድ የተደራጀ ነበር፤ ከላይ ከከፍተኛው ፉህረር (እራሱ ሂትለር) ጀምሮ ወደ ታች የትናንሽ ፉህረሮች ተዋረድ ይቀጥላል። የድርጅት ባለቤት የሱቅ ስራ አስኪያጅ (Betriebsführer) ነበር። የድርጅቱ ሰራተኞች ደግሞ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የፊውዳል ጌታዎች በነበራቸው ስያሜ ይጠራሉ፤ Gefolgschaft። እናም እነዚህ ሁሉ ሰዎች ስያሜው እጅግ በጣም ረጅም የሆነውን የReichsführerwirtschaftsministerium ተቋም ትዕዛዝ ማክበር ነበረባቸው። የዚህ ተቋም መሪ በጌጣጌጥ እና በሜዳሊያዎች ያጌጠው ታዋቂው ወፍራም ሰው ጎሪንግ ነበር።
እናም ከዚህ ባለ ረጅም ስያሜ የሚኒስትሮች አካል ነበር ለሁሉም የሀገሪቱ ድርጅት ትዕዛዝ የሚተላለፈው፡ ምን መመረት እንዳለበት፣ በምን ያህል ብዛት፣ ጥሬ እቃው ከየት መገኘት እንደሚችል እና ስንት መከፈል እንዳለበት፣ ምርት ለማን መሸጥ እንደሚችል እና በስንት ዋጋ። ሰራተኞችም የትኛው ፋብሪካ መስራት እንዳለባቸው ትዕዛዝ የሚቀበሉ ሲሆን መንግስት የወሰነውን ደመዎዝ ጭምር ይቀበላሉ። አጠቃላይ የኢኮኖሚ ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ተደርጓል።
የፋብሪካው መሪ(Betriebsführer) ትርፍ ለራሱ የመውሰድ መብት አለነበረውም። እሱም ደመዎዝ ተቀባይ ሲሆን ተጨማሪ ገንዘብ ካስፈለገው ለምሳሌ “በጣም ታምሜያለሁ፣ ወድያውኑ ቀዶ ጥገና ያስፈልገኛል፣ እናም ቀዶ ጥገናው አምስት መቶ ማርክ ያስከፍላል" በማለት ከተወሰነለት ደመዎዝ በላይ የማውጣት ጥያቄ ለቀጠናው መሪ (Gauführer) ማቅረብ ነበረበት። ዋጋ እና ደመዎዝ ትርጉማቸውን ያጡበት እና ትርጉማቸው ወደ ሶሻሊዝም ስርዓት መጠነ-ቃላት የተቀየሩበት ስርዓት ነበር።
ይህ ስርዓት እንዴት ሊፈርስ እንደቻለ ላስረዳቹህ። ከአመታት ውግያ በኋላ አንድ ቀን የውጭ ሀገር ጦር ኃይሎች ጀርመን ገቡ። ይህንን በመንግስት የሚመራውን የኢኮኖሚ ስርዓት ለማቆየት ሞክረው ነበር ነገር ግን እሱን ለመጠበቅ የሂትለርን ጭቆና መቀጠል ያስፈልግ ነበር። ያለዚህ ደግሞ አይሰራም።
እናም ይህ በጀርመን ሲካሄድ እያለ ታላቋ ብሪታንያ - በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቀት - የጀርመንን ፈለግ ተከተለች። የብሪታንያ መንግስት ከአንዳንድ ሸቀጦች የዋጋ ቁጥጥር ጀምሮ (ልክ ሂትለር በሰላም ግዜ ጀምሮ ሲያደርግ እንደነበረው) ደረጃ በደረጃ ኢኮኖሚውን በስፋት የመቆጣጠር ሂደት ከመጀመሩ የተነሳ ጦርነቱ ባበቃበት ግዜ የተጣራ ሶሻሊዝም ሊባል የሚችል ደረጃ ደርሰው ነበር።
ታላቋ ብሪታንያ ወደ ሶሻሊዝም የመጣቸው እ.አ.አ በ1945 በተቋቋመው የሰራተኛ(labour) ፓርቲ አልነበረም። ታላቋ ብሪታንያ ሶሻሊስት የሆነችው ዊንስተን ቸርችል ጠቅላይ ሚኒስተር በነበሩበት በጦርነቱ ግዜ ነው። ዊንስተን ቸርችልን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው የሰራተኞች ፓርቲ ቸርችል ያስተዋወቀውን የሶሻሊስት ስርዓት ነው ይዞ የቀጠለው። ይህም ሁኔታ በህዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶ ያለፈ ነው።
በታላቋ ብሪታንያ የተለያዩ ተቋማት በግልጽ በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋል(nationalization) ተጠናቅሮ ቢቀጥልም ፋይዳው እምብዛም ነበር፣ የባንክ ኦፍ ኢንግላንድ:: የእንግሊዝ ባንክ(Bank of England) በብሄራዊ ቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉ የይስሙላ ድርጊት ነበር ምክንያቱም ከዛም በፊት ባንኩ ሙሉ በሙሉ በመንግስት ትዕዛዝ ስር ስለነበር። የባቡር ዘርፍ እና በብረታ ብረት ኢንዱስትሪም ተመሳሳይ ሁኔታ አሳልፈዋል። “የጦርነት ሶሻሊዝም" ተብሎ እንደሚጠራው – ማለትም ደረጃ በደረጃ እያጠቃለለ የሚሄደው ጣልቃ ገብነት – ስርዓቱን ከሞላ ጎደል ወደ ብሄራዊ ስርዓት ቀይሮታል።
በጀርመን እና በብሪታን ስርዓቶች መካከል ያለው ልዩነት ከፈተኛ አለነበረም ምክንያቱም በሁለቱም ምሳሌዎች የስርዓቱ አስተዳዳሪዎች በመንግስት የተሾሙ እና በሁሉም ረገድ የመንግስትን ትዕዛዝ የማክበር ግዴታ ያለባቸው ነበሩ።
ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት የጀርመን የናዚ ስርዓት የካፒታሊስት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መለያዎችን እና ስያሜዎችን ይዞ ቆይቷል። ነገር ግን ትርጓሜያቸው በጣም የተለየ ነበር፤ የመንግስት ድንጋጌ ብቻ ነበር።
የብሪታንያም እውነታ ተመሳሳይ ነበር። የወግ አጥባቂ ፓርቲ (conservative party) ወደ ስልጣን ሲመለስ የተወሰኑ ቁጥጥሮችን አስወግዷል። በታላቁ ብሪታንያ በአሁኑ ግዜ በአንድ ጎን ቁጥጥሮችን ለማቆየት በሌላ ጎን እነሱን ለማጥፋት የሚደረጉ ሙከራዎች አሉ። (ነገር ግን በእንግሊዝ ያለው ሁኔታ ሩስያ ከምትገኝበት ሁኔታ በጣም የተለየ መሆኑ መረሳት የለበትም።) ይህ ተመሳሳይ ሁኔታ ምግብና ጥሬ እቃ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ምርት እያመረቱ ወደ ውጭ መላክ ባለባቸው አገሮች ያለ ነው። በወጪ ንግድ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጥገኛ ለሆኑ አገሮች የመንግስት ቁጥጥር ስርዓት በፍጹም አይሰራም።
ስለዚህ፣ የኢኮኖሚ ነጻነት እስካለ ድረስ ሊኖር የሚችለው የወጪ ንግድን ማቆየት አስፈላጊ በመሆኑ ነው። (እንደ ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ስዊድን ያሉ አገሮች አሁንም ጠንካራ የሚባል ነጻነት አለ)። ቀደም ሲል የወተትን ምሳሌ የመረጥኩት ለወተት የተለየ ምርጫ ስላለኝ ሳይሆን በቅርብ አሥርተ አመታት ሁሉም መንግስት በሚያስብል ደረጃ (አብዛኞቹ) የወተትን፣ የእንቁላል እና የቅቤ ዋጋን መቆጣጠር በመጀመራቸው ነው።
የኪራይ ቁጥጥር
ወደ ሌላ ምሳሌ በመሄድ ጥቂት ቃላት ማለት እፈልጋለሁ፣ እሱም ኪራይ ቁጥጥር ነው። መንግስት የቤት ኪራይ ሲቆጣጠር አንዱ ውጤት የቤተሰባቸው ሁኔታ ሲለወጥ ከትላልቅ ወደ ትናንሽ አፓርታማዎች በራሳቸው ግዜ ይሸጋገሩ የነበሩ ሰዎች ይህን ማድረግ ያቆማሉ። ለምሳሌ እድሜያቸው ወደ ሃያዎቹ በመጠጋቱ፣ ትዳር በመያዛቸው ወይም ለስራ ወደ ሌላ ከተማ በመሄዳቸው ልጆቻቸው ቤታቸውን ለቀው ስለሚሄዱ ወላጆች እናንሳ። ይህንን ሁኔታ የሚያሳልፉ ወላጆች መኖርያቸውን አነስ ብሎ ረከስ ወዳለ ቤት ወይም አፓርታማ ይቀይሩ ነበር። የቤት ኪራይ ዋጋ ቁጥጥር ሲጀመር ይህን የማድረግ ግዴታ ጠፋ።
የኪራይ ቁጥጥር በደንብ በሰፈነባት የቀደምት 1920ዎቹ ቪየና፣ ኦስትሪያ አንድ የቤት ባለንብረት ኪራይ ከተተመነበት ከአንድ ተራ አፓርታማ የሚያገኘው ገንዘብ፣ አንድ ግዜ በከተማ መኪና ለመሳፈር ከሚከፍለው የቲኬት ዋጋ በእጥፍም የማይበልጥ ነበር። ሰዎች አፓርታማ ለመለወጥ ምንም የሚያስገድዳቸው ነገር እንዳልነበረ ለማሰብ አይከብድም። በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ ቤቶች ግንባታ አልነበረም። በዩናይትድ ስቴትስ ሁለተኛውን የአለም ጦርነት ተከትሎ ተመሳሳይ ሁኔታ የሰፈነ ሲሆን፣ እስከዛሬ በብዙ ከተሞች ቀጥሎ ይታያል።
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያሉ በርካታ ከተሞች በከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ውስጥ ከሚገኙባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የኪራይ ቁጥጥር እና የሚያስከትለው የመኖሪያ ቤት እጥረት ነው። ስለዚህ መንግሥት ለአዳዲስ ቤቶች ግንባታ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥቷል። ግን ለምን የዚህ አይነት የመኖርያ ቤት እጥረት ተፈጠረ? የመኖርያ ቤት እጥረት የሚፈጠርበት ምክንያት የወተት ቁጥጥር ሲኖር የወተት እጥረት ከሚፈጠርበት ምክንያት ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ ማለት፤ መንግስት በገበያ ውስጥ ጣልቃ ሲገባ ቀስ በቀስ ወደ ሶሻሊዝም እያመራ ይሄዳል።
ይህ እውነታ እንደሚከተለው አይነት ጥያቄ ለሚያቀርቡ ሰዎች መልስ ነው፣ “እኛ ሶሻሊስቶች አይደለንም፣ መንግስት ሁሉንም ነገር እንዲቆጣጠር አንፈልግም። እሱ መጥፎ እንደሆነ እንረዳለን። ነገር ግን መንግስት በተወሰነ ደረጃ ገበያ ውስጥ ለምን ጣልቃ አይገባም? አንዳንድ የማንፈልጋቸውን ነገሮች መንግስት ጣልቃ እየገባ ለምን አያስወግድም?”
የአጋማሽ መንገድ ስርዓት አለ?
እነዚህ ሰዎች ስለ “አጋማሽ መንገድ" ፖሊሲ ያወራሉ። የማይታያቸው ነገር ግን የተናጠል ጣልቃ ገብነት - ማለትም በኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ በተወሰነ መልኩ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት - የመጨረሻ ውጤት(በራሱ በመንግስት መስፈርት) ሊቀርፍ ከተነሳው ችግር የባሰ ሁኔታ ማምጣቱን ነው፣ የቤት ኪራይ ዋጋ ቁጥጥር ሲጠይቁ የነበሩ ሰዎች መጨረሻ ላይ የቤት እና የአፓርታማ እጥረት መፈጠሩን ሲያውቁ በጣም ይበሳጫሉ።
ነገር ግን ይህ የመጠለያ እጥረት የተፈጠረበት ዋነኛ ምክንያት በመንግስት ጣልቃ ገብነት እና በነጻ ገበያው ሰው ይከፍል ከነበረው ዋጋ የወረደ ዋጋ በመደንገጉ ነው።
በሶሻሊዝም እና በካፒታሊዝም መሃል የሚገኝ እና እንደ ደጋፊዎቹ አገላለጽ ከሁለቱም ስርዓቶች በእኩል ርቀት የሚገኝና የሁለቱንም ጥቆም ይዞ ጉዳታቸውን የሚያስቀር ሶስተኛ ስርዓት አለ የሚለው ሃሳብ ከናካቴው ከንቱ የሆነ ሃሳብ ነው። የዚህ አይነት ምናባዊ ስርዓት አለ ብለው የሚያምኑ ሰዎች የጣልቃ ገብነትን ክብር ሲያወድሱ እስከ ቅኔያዊነት ይደርሳሉ። ነገር ግን ተሳስተዋል ማለት ይቻላል። የሚያሞካሹት የመንግስት ጣልቃገብነት እራሳቸው የማይወዱትን ሁኔታ ያመጣል።
ከችግሮቹ መሃከል አንዱ በኋላ የማነሳው ሲሆን እሱም ፕሮቴክሽኒዝም ነው። መንግስት የአገር ውስጥ ገበያን ከዓለም ገበያ ለማግለል ይሞክራል። የአንድን ምርት የአገር ውስጥ ዋጋ ከዓለም ገበያ ዋጋ በላይ ከፍ የሚያደርግ የገቢ ቀረጥ ያስተዋውቃል፣ ይህም የአገር ውስጥ አምራቾች ወደ ካርቴልነት እንዲቀየሩ ያደርጋል። ይህንንም ተከትሎ “በዚህ ሁኔታ የፀረ-ካርቴል ህግ አስፈላጊ ነው" በማለት መንግስት ካርቴሎቹን ያጠቃል።
ይህ ሁኔታ አብዛኞቹ የአውሮፓ መንግስታት ከሚገኙበት ሁኔታ ፍጹም ተመሳሳይ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ለፀረ-ሞኖፖል ህጎች እና በሞኖፖላዊ አደጋ ላይ መንግስት ላወጀው ዘመቻ ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች አሉ።
በገዛ ጣልቃ ገብነቱ የአገር ውስጥ ካርቴሎች እንዲፈጠሩ የሚያስችለውን ሁኔታ ከፈጠረ በኋላ መንግስት በንግድ ማህበረሰብ ላይ ጣቱን ቀስሮ “ካርቴሎች አሉ፣ ስለዚህ በንግድ ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ነው" ሲል ማየት ዘበት ነው። ይልቅ መንግስት ለካርቴሎቹ መፈጠር ምክንያት የሆነውን የገበያ ጣልቃ ገብነት በመግታት ካርቴል ማስቀረት በአንጻሩ ይቀላል።
የመንግስት ጣልቃ ገብነት ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ነው የሚለው ሃሳብ በእያንዳንዱ ሀገር ውስጥ ሲያንስ አጥጋቢ ወዳልሆነ፣ ሲብስ ደግሞ ከፍተኛ ትርምስ ወዳለው ሁኔታ የሚወስድ ነው። መንግስት በወቅቱ ካላቆመው ሶሻሊዝም ይመጣል።
ይሁን እንጂ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አሁንም በጣም ድጋፍ ያለው ነገር ነው። አንድ ሰው ዓለም ላይ የማይወደውን ነገር ሲያስተውል እንዲህ ይላል፡ “መንግስት አንድ ነገር ማድረግ አለበት። ለዚህ ካልሆነ መንግስት ለምኑ ነው ያለን? መንግስት መፈፀም አለበት"። ይህ ደግሞ ከዘመናዊ ነጻነት፣ ከዘመናዊ ህገመንግስታዊ መንግስት፣ ከዘመናዊ ተወካይ መንግስት እና ከዘመናዊ የሪፐብሊካኒዝም መንግስት በፊት የነበሩ የጥንት አስተሳሰቦች መገለጫ ነው።
ለብዙ መቶ ዘመናት አንድ ንጉሥ ማለትም ቅቡዕ ንጉሥ የአምላክ መልእክተኛ እንደሆነ፣ ከተገዢዎቹ የበለጠ ጥበብ እንዳለውና ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ኃይል እንዳለው የሚገልጸው ትምህርት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር።
የአስራዘጠነኛው ክፍለዘመን ያህል የቀረበ ግዜ ድረስ በተወሰኑ በሽታዎች የሚሰቃዩ ሰዎች በንጉሳዊ ንክኪ ወይም በንጉስ እጅ የመፈወስ ተስፋ ነበራቸው። ዶክተሮች በተለምዶ የተሻሉ ነበሩ፤ ያም ሆኖ ታካሚዎቻቸው ንጉሱን እንዲሞክሩ ይገፋፉ ነበር።
ይህ የአባታዊነት ባህሪ ስላለው መንግስት፣ ከተፈጥሮ እና ከሰው ልጅ በላይ ሃይል ስላላቸው የዘውድ ነገስታት የሚተርከው አስተምህሮ በግዜ ሂደት ጠፋ - ወይም ቢያንስ እንደዛ ብለን አስበን ነበር። ግን እንደገና ተመልሶ መቷል። ቨርነር ሶምባርት የተባለ በዓለም ዙርያ የታወቀ፣ የብዙ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክተር እና የአሜሪካ ኢኮኖሚ ማኅበር የክብር አባል የሆነ አንድ ጀርመናዊ ፕሮፌሰር ነበር(በቅርብ አውቀዋለሁ)። ይህ ፕሮፌሰር በፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተተረጎመ መጽሐፍ ጽፈዋል። በተጨማሪም በፈረንሳይኛ ምናልባትም በስፓኒሽ ቋንቋ ተተርጕሞ ይገኛል – ቢያንስ እንደሚገኝ ተስፋ አደርጋለሁ፣ ምክንያቱም ያኔ የምናገረውን ማረጋገጥ ትችላላችሁ። የኤኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ቨርነር ሶምባርት በጨለማው ዘመን ሳይሆን በዘመናችን በታተመው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ ይጽፋሉ፦ “Führer, የኛ Führer” - በእርግጥ ሂትለር ማለት ነው - “ትዕዛዙን በቀጥታ የሚያገኘው ከአምላክ ነው፣ የጽንፈ አለሙ Führer”። ቀደም ሲል ስለዚህ የፊውረሮች ተዋረድ ተናግሬ ነበር፣ እናም በዚህ የስልጣን ተዋረድ ሂትለርን “የላዕላይ ፊውረር" ብዬ ጠርቼዋለሁ …ይሁን እንጂ እንደ ቨርነር ሶምባርት ከሆነ ከዚያ ልቆ የተቀመጠ ፊውረር አለ፤ ይኸውም የአጽናፈ ሰማይ ፊውረር የሆነው አምላክ። አምላክ ደግሞ ትእዛዙን በቀጥታ የሚሰጠው ለሂትለር እንደሆነ ጽፏል። እርግጥ ነው ይላል ፕሮፌሰር ሶምባርት ሳይደፍር፦ “አምላክ ከፊውረሩ ጋ እንዴት እንደሚነጋገር አናውቅም። ይሁን እንጂ እውነታውን መካድ አይቻልም።”
እንግዲህ ይህን አይነት መጽሐፍ በአንድ ግዜ የፈላስፋዎች እና የገጣሚዎች ሀገር ተብሎ በሚታወቀው የጀርመን ህዝብ ቋንቋ ተጽፎ ለእትም መብቃቱን ስትሰሙ፣ ከዛም አልፎ ወደ እንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ ተተርጉሞ ሲታተም ስታዩ፣ ትንሹ ቢሮክራት እንኳ እራሱን ከዜጎች የበለጠ ጥበበኛ እና የተሻለ አድርጎ በመቍጠር በሁሉም ነገር ጣልቃ መግባት የሚፈልግ መሆኑ አይገርምም። ምንም እንኳ እሱ ምስኪን ትንሽ ቢሮክራት እንጂ ታዋቂው ፕሮፌሰር ሶምባርት የሁሉም ነገር የክብር አባል ባይሆንም።
እንደዚህ አይነት ክስተቶችን ለመከላከል መፍትሄ አለ? አዎ እላለሁ፣ መድሃኒት አለ።እናም ይህ መድሃኒት የዜጎች ኃይል ነው፤ ከተራው ዜጋ ከፍ ያለ ጥበብ ለራሱ የሚመድብ እንደዚህ አይነት አምባገነናዊ አገዛዝ እንዳይመሰረት መከላከል አለባቸው። በነጻነትና በባርነት መሃከላ ያለው መሰረታዊ ልዩነት ይህ ነው።
የሶሻሊስት ሃገራት ዴሞክራሲ የሚለውን ቃል ለራሳቸው አጎናጽፈዋል። ሩስያውያን የራሳቸውን ሥርዓት የሕዝብ ዴሞክራሲ በማለት ይጠሩታል፤ እነሱ ምናልባት ሕዝቡ በአምባገነኑ ምስል ይወከላል ብለው ያምናሉ። እኔ እንደማስበው ከሆነ ግን እዚህ አርጀንቲና ውስጥ ሁዋን ፔሮን የተባለው አምባገነን በ1955 የግዳጅ ስደት ሲላክ ጥሩ መልስ ተሰጥቶት ነበር። በሌሎች ሀገሮች ያሉ ሌሎች አምባገነኖች ሁሉ ተመሳሳይ ምላሽ ይሰጣቸዋል ብለን ተስፋ እናድርግ።