መግብያ
ለዛሬም ሆነ ለነገ ተስማሚው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀላል ነው። መንግስት በግዛቱ ስር የሚኖሩ ሰዎችን ህይወት እና ንብረት ከሀገር በቀል እና ከውጭ ሀይል ጥቃት መጠበቅ እና መከላከል አለበት፣ የሚፈጠሩ ጠቦችን መፍታት አለበት፤ ከዛ በተረፈ ግን ሰዎች የራሳቸውን ግብ እና አላማ እንዲያሳድዱ በነጻነት ሊተዋቸው ይገባል። ይህ ሀሳብ አሁን ከምንኖርበት የመንግስት ጣልቃ ገብነት ዘመን አንጻር ስር ነቀል ለውጥ ነው። በአሁን ዘመን መንግስታት የምርት ሂደትን እንዲከታተሉ እና እንዲቆጣጠሩ፣ የተወሰኑ ምርት እና አገልግሎቶች ላይ ዋጋ እንዲጨምሩ ወይም እንዲቀንሱ፣ የደሞዝ መጠን እንዲወስኑ፣ የተወሰኑ ድርጅቶችን በመቋቋም እንዲረዱ እና ሌሎችን ደግሞ ከኪሳራ እንዲከላከሉ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ እና ወደ ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን እንዲያበረታቱ ወይም እንዲገድቡ፣ የታመሙ እና እድሜ የተጫናቸውን እንዲረዱ፣ አባካኞችን እንዲደግፉ እና ወዘተ ይጠየቃሉ።
ለሀገር ተስማሚ የሆነው መንግስት ግን ሊንከባከብ የሚገባው ሰዎችን ሳይሆን ግለሰቦች፣ አምራቾች፣ ነጋዴዎች፣ ሰራተኞች፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ ቆጣቢዎች እና ተጠቃሚዎች ሁሉ አላማቸውን ሊያሳኩ የሚሮጡበትን ስርአት ነው። መንግስት ከዚህ አላማ ዝንፍ ሳይል ይህን ማድረግ ከቻለ መንግስት ሊያደርግላቸው በማይችለው መጠን ሰዎች እራሳቸውን መርዳት ይችላሉ። ፕሮፌሰር ሉድዊግ ቮን ሚዝስ በዚህ አጭር መጸሃፍ የሚያስተላልፉት አንኳር መልእክት ይህ ነው።
እ.አ.አ ከ1881-1973 የኖረው ፕሮፌሰር ሚዝስ ሀያኛው ክፍለዘመን ካፈራቸው ቀዳሚ ኢኮኖሚስቶች መሃል ተጠቃሽ ነው። እንደ Human Action፣ Socialism፣ Theory and History እና ሌሎች በርካታ በጥልቀታቸው የሚታወቁ መጸሃፎችን ጽፏል። ነገር ግን እ.አ.አ በ1959 በአርጀንቲና ያደረጋቸውና በዚህ መጽሃፍ ተቀርጸው የተቀመጡት ንግግሮች በቴክኒካዊ ቃላት የተሞሉ ሳይሆን በግዜው ታዳሚ የነበሩት የንግድ ባለሙያዎች፣ ፕሮፌሰሮች፣ አስተማሪ እና ተማሪዎች በሚረዱት መልክ የቀረቡ ናቸው። ንድፈ ሃሳቦችን በቤተኛ ቋንቋ መግለጽ ችሏል። ቀላል የታሪክ እውነታዎችን በምጣኔ ሀብት መርሆች ያስረዳል። ካፒታሊዝም የተዋረዳዊውን ፊውዳሊዝም ስርአት እንዴት እንዳጠፋው እና የተለያዩ የመንግስት አወቃቀሮች ስለሚፈጥሩት ፖለቲካዊ ምህዳር ያስረዳል። የሶሻሊዝም እና የማህበራዊ ደህንነት መንግስት ውድቀቶችን ከመመርመር አልፎ ሰራተኞች እና ሸማቾች ካፒታሊዝም በሚሰጣቸው የራስን እጣ ፈንታ በመወሰን ነጻነት ሊያሳኳቸው ስለሚችሉት ነገሮች ያብራራል።
የሌሎችን ነጻነት ሳይነኩ ኑሯቸውን በነጻነት መምራት የሚፈልጉ ግለሰቦችን መብት የሚጠብቅ መንግስት ሲኖር፣ ሰዎች በተፈጥሮ የሚቀሏቸውን ነገሮች(ስራ መስራት፣ መተባበር፣ በንግድ መተሳሰር) ማከናወን ይጀምራሉ። ይህ ሁኔታ ለሚቆጥቡ፣ ካፒታል ለሚያከማቹ፣ ፈጠራ ለሚፈጥሩ፣ ሙከራ ለሚያካሂዱ፣ እድሎችን ለሚጠቀሙ እና ምርት ለሚያመርቱ ልዩ ማበረታቻ ይፈጥራል። በዚህ ሁኔታ ካፒታሊዝም እያደገ ይመጣል። ፕሮፌሰር ሚዝስ እንደሚያስረዳው የ18ኛው እና የ19ኛው ክፍለዘመን አስደናቂ ኢኮኖምያዊ ለውጥ እና የሁለተኛው አለም ጦርነት መገባደድን ተከትሎ በጀርመን የታየው ኢኮኖሚያዊ ተአምር የካፒታሊዝም ውጤቶች ናቸው፡
ነገር ግን ማስታወስ ያለብን ነገር ቢኖር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጉዳይ የተለየ ተአምር ያለው ነገር አለመሆኑን ነው። የጀርመን ኢኮኖሚያዊ ተአምር ተብሎ ስለሚገለጸው የሁለተኛው አለም ጦርነት ውድመትን ተከትሎ ጀርመን ስላስመዘገበችው ማንሰራራት በተመለከተ በጋዜጦች ብዙ አንብባችኋል። ይህ ግን ተአምረኛ ነገር አይደለም። የነጻ ገበያ ኢኮኖሚያዊ መርሆች አተገባበር ውጤት ነው፣ የካፒታሊዝም መንገድ ውጤት ነው(ምንም እንኳ ካፒታሊዝም ሙሉ በሙሉ እና በሁሉም ረገድ የተተገበረ ባይሆንም)። ሁሉም ሀገር ተመሳሳይ ኢኮኖሚያዊ “ተዓምር” ማሳለፍ የሚችል ሲሆን አስረግጬ ሳልናገር የማላልፈው ነገር ቢኖር ይህ ለውጥ የተአምር ውጤት ሳይሆን ከተስማሚ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች መተግበር የተቀዳ ውጤት መሆኑን ነው።
ግለሰቦች የራሳቸውን ግቦች የሚከተሉበት እና ከጎረቤቶቻቸው በሰላም የሚኖሩበትን ተስማሚ ሁኔታ በመፍጠር የተገደበ መንግስት ሲኖር ተስማሚ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተፈጥሯል ማለት እንችላለን። የመንግስት ግዴታ በቀላሉ የሰዎችን ህይወት እና ንብረት መጠበቅ እና ሰዎች በነጻነት ተባብረው እና በንግድ ተሳስረው የሚኖሩበትን እድል መፍጠር ነው። በዚህ ሁኔታ መንግስት ካፒታሊዝም የሚለመልምበትን የኢኮኖሚያዊ ምህዳር ይፈጥራል፡
የካፒታሊዝም ጉልብትና ፋይዳ ሰው ሁሉ ደንበኛውን በተሻለ ሁኔታ እና በተሻለ ዋጋ የማገልገል መብት ሲኖረው ነው። ይህ መንገድ ወይም መርህ አጭር በሚባል ግዜ ውስጥ አለምን መቀየር ችሏል። ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የአለምን ሰዎች ብዛት መጨመር ችሏል።
መንግስት ከዚህ በላይ የመስራት ሀይል እና ስልጣን በሚጎናጸፍበት ግዜ እና በታሪክ ብዙ ግዜ እንዳየነው ስልጣኑን አላግባብ በሆነ ሁኔታ ሲጠቀም(የሂትለር ጀርመን፣ የስታሊን ሶቭየት ህብረት፣ የፔሮን አርጀንቲና ተጠቃሽ ናቸው) የካፒታሊዝም ስርአትን የሚያናጋ እና ለሰው ልጅ ነጻነት አጥፊ ሀይል ይሆናል።
ሚዘስ አርጀንቲናን እ.አ.አ በ1959 ዓ.ም ሲጎበኝ በ1946 የሀገሪቱ ፕሬዝደንት በመሆን ተመርጦ የነበረው አምባገነኑ ሁዋን ፔሮን በ1955 ዓ.ም ከሀገሩ ተገፍቶ ወጥቶ በስደት ላይ ነበር። በህዝቡ ተወዳጅ የነበረችው የፔሮን ሚስት ኤቫ ቀደም ብላ እ.አ.አ በ1952 ዓ.ም ሙታ ነበር። ምንም እንኳ ፔሮን ስደት ላይ የነበረ ቢሆንም በሀገሪቱ ብዙ ደጋፊ ነበረው፤ በፖላቲካውም ትልቅ ተቀናቃኝ ሀይል ነበር። በ1973 ዓ.ም ወደ ሀገሩ አርጀንቲና በመመለስ ድጋሚ ፕሬዝዳንት ሁኖ መመረጥ የቻለ ሲሆን፣ የሀገሩ ምክትል ፕሬዝደንት መሆን ከቻለችው አዲስ ሚስቱ ኢዛቤሊታ ጋር ሀገሩን እስከለተ ሞቱ ለ10 ወር ማስተዳደር ችሏል። የሱን ሞት ተከትሎ ኢዛቤሊታ አስተዳደሯ በሙስና ተከሶ ከስልጣን እስከወረደበት እስከ1976ዓ.ም ድረስ የሀገሩ መሪ ሁና መቀጠል ችላለች። እሷን ተከትሎ ተከታታይ ፕሬዝደንቶች የነበራት አርጀንቲና የኢኮኖሚ ሁኔታዋን ለማሻሻል እርምጃዎችን ወስዳለች። ህይወት እና ንብረት የተሻለ ክብር አግኝተዋል ፣ የተወሰኑ ብሄራዊ ኢንዱስትሪዎች ወደ ግል ይዞታ ተሸጋግረዋል፣ ኢንፍሌሽንም በመጠኑም ቢሆን እንዲቀንስ ተደርጓል።
ይህ መጽሀፍ የሚዝስን ሀሳቦች ለመረዳት እንደ ጥሩ ጅምር ያገለግላል። የሚዝስ ሀሳቦች Human Action በሚለው መጽሃፉ እና በሌሎች ምሁራዊ ስራዎቹ በስፋት ተዳሰዋል። ለሱ ሃሳቦች አዲስ የሆኑ ሰዎች ግን Bureaucracy እና The Anti-Capitalistic Mentality በተባሉት ቀለል በሚሉ መጽሃፎቹ ቢጀምሩ ተስማሚ ይሆናል። ይህ ጅማሮ አንባቢዎች ሚዝስ በትልቅ ስራዎቹ ስላቀረባቸው የነጻ ገበያ መርሆች እና ኢኮኖሚያዊ ንድፈ ሃሳቦች ለመረዳት ጥሩ መሰረት ይኖራቸዋል።
ቤቲና ቢየን ግሪቭስ እ.ኤ.አ ፌብሩዋሪ 1995ተጨማሪ
በ1995 የጠቀስኩት አርጀንቲና ወደ ነጻ ገበያ የወሰደችው እርምጃ በአሳዝኝ ሁኔታ ዘላቂ አልነበረም። የመንግስታትና እና ፕሬዝዳንቶች ተደጋጋሚ መለዋወጥ ኢንፍሌሽን እና የመንግስት ኢኮኖሚያዊ ጣልቃ ገብነት ወደ አርጀንቲና ይዞ መቷል።
ቤቲና ቢየን ግሪቭስ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2006